አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 29፤2012

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ከገለፀበት ጊዜ ጀምሮ  መንግስት የተለያዩ አማራጮችን በህግ ባለሙያዎች ሲያስጠና መቆየቱን በመግለፅ፥ የህግ ባለሙያዎችም ምርጫው መተላለፍ የሚችልበትን የህግ አማራጮችን ማቅረባቸውንና በዚህም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ገልጸዋል።

የቀረቡትን አማራጮች ተከትሎ በርካቶች የተለያየ ሀሳብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ገንቢ ሀሳብ ለሚያቀርቡት ምስጋና አቅርበው፤ ሆኖም ግን አማራጮቹ ተቀባይነት የላቸውም፣ ህገ መንግስቱ የሚተረጎም አንቀጽ የለውም በሚል የሽግግር መንግስት ሀሳብ ያቀረቡ መኖራቸውንም አንስተዋል።

ህገ መንግስቱ የሚተረጎም አንቀጽ የለውም የሚለው ክርክር አውቆ ላለማወቅ ከወሰነ አካል ወይም ጥልቅ የሆነ አላዋቂነት ውስጥ ከተዘፈቀ ሰው የሚቀርብ ሀሳብ መሆኑንም ጠቅሰዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አክለውም አሁን ያለው መንግስት ህግ የሚያወጣ፣ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን የሚፈርም፣ በጀትና እቅድ የሚያፀድቅ ህጋዊ መንግስት መሆኑን በመጥቀስ፤ ብልፅግና ፓርቲም በመላ ሀገሪቱ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መዋቅር ያለው፣ ሀገራዊ ለውጡን በመምራት የበርካቶችን ድጋፍ ያገኘ ግዙፍ ፓርቲ ነውም ብለዋል።

ያለ ምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ስልጣን የመከፋፈል ህጋዊም ሆነ ህገ መንግስታዊ አግባብ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣን ይገባኛል የሚለው ፈሊጥ ዴሞክራሲያዊም ህገ መንግስታዊም አይደለም ሲሉ ገልጸዋል ህገ መንግስቱ ከደነገገው ውጪ በህገወጥ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመግለፅ፤ እንዲህ አይነቱ እንቅሰቃሴ የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሀገሪቱንና ዓለም አቀፍ ህጎችን የሚጥስ መሆኑንም አስታውቀዋል የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 50 የፌደራል መንግስት ስልጣንና ተግባር ሲዘረዝር ቁጥር አንድ አድርጎ ያስቀመጠው ህገ መንግስቱን የመጠበቅና የመከላከል ኃላፊነት ነው፤ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ሲሉም ገልፀዋል።