አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 29፤2012

ጠ/ሚ ዐቢይ ህገ – መንግሥቱ ከደነገገው ውጭ ያለ ምርጫ እንዲሁም በህገ ወጥ ምርጫ ስልጣን እቆናጠጣለሁ ብሎ የሚያስብ አካል የሃገሪቱንም ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ድንጋጌዎችን እንደሚጥስ ከመጠቆም በተጨማሪ መንግሥታቸው እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል የሀገሪቱ መሪ አክለውም “ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣን ካልሰጣችሁኝ አገር አተራምሳለሁ የሚለውን ማንኛውንም ኃይል አንታገስም፤ በቂ ዝግጅትም አለን” ብለዋል የፌደራል መንግሥቱ ዋነኛ ኃላፊነት ህገ መንግሥቱን የመጠበቅና የመከላከል ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑንም ገልፀው፤ ይህንን ተግባራዊ በማያደርጉና ምስቅልቅሉ የወጣ ምርጫ ለማድረግ እንነሳለን በሚሉም ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ መንግስታቸው እንደሚገደደም ዶ/ር ዐቢይ በአፅንኦት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት መሰረት መንግሥት ለመመስረት ምርጫ ግዴታ እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ሳይካሄድ ስልጣን ላይ መውጣት ህጋዊ መሰረትም የለውም ብለዋል “የፖለቲካ ፓርቲ ስለሆንኩ ስልጣን ይገባኛል የሚለው ፈሊጥ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ህገ መንግሥታዊ አካሄድ አይደለም፤ ያለ ምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ስልጣን የሚከፋፈልበት ሁኔታም አያስሄድም” ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ ያስጠነቀቁትን አካል በስም ባይጠሩም በአጠቃላይ ንግግሩ ጠቅሶናል የሚሉ አካላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል በተለይም ከጠ/ሚሩ መልዕክት የደቂቃዎች ልዩነት በኋላ የትግራይ ክልል ም/ር/ መስተዳደር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የህዝብ ወሳኝነት ለትንሽም ጉዳይ ቢሆን ለድርድር እንዲቀርብ አንፈቅድም፣ አይገባምም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ደብረጽዮን እንደ ህዝብ የታገልነው የህዝብን የመወሰን መብት ለማረጋገጥ፣ ሁለንተናዊ ፍትህና ነጻነት እውን ለማድረግ ነው ያሉ ሲሆን  ህዝብ በመረጠው እንዲዳኝ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ ህዝብ ባመነበት ህግና ስር ዓት እንዲተዳደር፣ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል አካሄድ ፍትህና ርትእ በማናወጥ ይደረግ የነበረው ሁሉን አይነት እንቅስቃሴ ለማቆም ነው ሲሉም ገልጸዋል በመሳሪያ ትግል በተጋድሎችን እንደተረጋገጠው ህዝብ ያላመነበትና ያልመከረበት ማንኛውም እንቅስቃሴ የትም እንደማይደርስ ነው የሚሉት ዶ/ር ደብረጽዮን  የመሳሪያ ትግሉም ለድል እንዲበቃ ካስቻሉን ምክኒያቶች ውስጥ በእያንዳንዱ የትግል መድረክ ህዝብ የሚሳተፍበትና የሚወስንበት መድረክ ስለነበረን ነው የሚል ንግግር አስከትለዋል።

አክለውም ሁሉም የትግራይን ህዝብ የሚወድና የሚያከብር በትግላችን የተከልነውን ስርዓት ሊያከብርና እንዲከበር ሊደረግ ይገባል የሚል መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በማንኛውም ምክኒያት ይህን ሃሳብ የሚጻረር ሃሳብም ሆነ ተግባር በጥብቅ ልንታገለው ይገባል የሚል ሀሳብ አስፍረዋል ም/ርዕሰ መስተዳደሩ ከዚህ በተጻራሪ የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ክብር አሳልፎ የሚሰጥን እንታገላለን ያሉ ሲሆን በመዘበራረቅ የሚፈታ ችግር የለም፤ እንደውም ችግሩ እንዳይፈታ የበለጠ ችግር መፍጠር ነው የሚሆነው የሚል ማሳሳቢያም ጨምረውበታል በመጨረሻም በሁሉም እንቅስቃሴዎቻችን  በንቃትና በብስለት እየመዘን ልንጓዝ ይገባል የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡