አባይ ሚዲያ ግንቦት 08፤2012

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ስም ከጥቂት ቀናት በፊት ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት የተላከው ሰነድ የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ዲሞክራሲ ፓርቲ /ኢሶዴፓን እንደማይመለከተው የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አስታውቀዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ከአባይ ሚዲያ ጋር ባድረጉት ቆይታ ከአባል ድርጅቶቹ መካከል ሶስቱ በሰነዱ ላይ ስምምነታቸውን በማረጋገጣቸው ኢሶዴፓ የራሱን መግለጫ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰር  በየነ በፓርቲያቸው ውስጥ ቀደም ሲል ሲነጋገሩበት የነበረውና አሁን ለገባንበት ችግር መፍትሄ መፈለግ ያለበት ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን በዚህ መሰረትም ምርጫን ለማራዘምና አሁን ላለንበት ችግር መፍትሄው የህገ መንግስት ትርጓሜ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ አንድነት ንቅናቄ /ሲአን/ እና አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲዎች ቀደም ሲል ከኛ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ሲገልጹ እነደቆዩ ፐሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

የመድረክ አባል የሆኑት ሶስት ድርጅቶች ምናልባትም በኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር  መረራ ጉዲና  ጫና በሰነዱ ላይ ሳይስማሙ እንዳልቀረ የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ  በቀጣይ ከኦፌኮ ጋር ለመስራት እንደሚቸገሩና የጥምረቱን ማዕከላዊ ኮሚቴ መጥራትና መነጋገር ግድ እንደሚል አስታውቀዋል።

ኦፌኮ ከመድረክ ጋር አጋር ሆኖ እያለ በተለያዩ  ሰባት የፖለቲካ ፓረቲዎች በአቋቋሙት ትብብር ውስጥ መግባቱን ገልጸው ፤አሁን ደግሞ በመድረክ ስም ሰነድ ማዘጋጀቱ ተገቢ አለመሆኑን ፐሮፌሰር በየነ አስረድተዋል፡፡