አባይ ሚዲያ ግንቦት 09፤2012

‹‹በቀን አንድ ዶላር›› በማዋጣት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ድጋፍ እንዲሰጡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አነሳሽነት የተመሠረተው የኢትየጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ፣ በቦርድ አመራሮች ውዝግብ የህልውና አደጋ ውስጥ መውደቁ ተሰማ በቦርድ ዳይሬክተሮች የሚመራው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በአባላቱ መካከል ውዝግብ መነሳት የጀመረው ካሰባሰበው የስድስት ሚሊዮን ዶላር ውስጥ አምስት ሚሊዮን ዶላር በመመደብ፣ ከ22 ፕሮጀክቶች ውስጥ ለአምስቱ ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት አድርጎ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ሒደት ውስጥ ተከሰቱ በተባሉ የሥነ ምግባርና ሌሎችም በርካታ ከአሠራር ያፈነገጡ ተግባራት ምክንያት፣ የተቋሙ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በመግለጽ ደብዳቤ ይጽፋሉ እንደ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ሁሉ የእሳቸው ምክትል የሆኑት (ዶ/ር) ምሕረት ማንደፍሮ እና የቦርድ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ፍቅሬ ዘውዴም ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ መልቀቂያ ካስገቡ በኋላ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፣ አሜሪካ የሚገኙትን አቶ ዮሐንስ አሰፋን በቦርድ ሊቀመንበርነት ይሾማል ነገሮች በዚህ መስመር ሲጓዙ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ አቶ ዮሐንስ የተመረጡበት የስብሰባ አጀንዳ፣ የተያዘው ቃለ ጉባዔና ድምፅ የተሰጠበትን አግባብ ገምግሞ ሒደቱን ውድቅ በማድረግ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ሕጋዊ ዕውቅናና ተቀባይነት ያላቸው በመሆናቸው፣ አግባብነት ባለው ምርጫ ሥርዓት እስካልተተኩ ድረስ በኃላፊነታቸው እንዲቆዩ በመጠየቅ እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡

ለማኅበራት ዕውቅናና ፈቃድ የመስጠትና የመሰረዝ ሥልጣን ለተሰጠው የበጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ በተቋቋመበት አዋጅ መሠረት የበጎ አድራጎት ማኅበራት የአመራርና የአሠራር ለውጥ ሲያደርጉ ማሳወቅ እንደሚጠቅባቸው፣ ይህ በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በኩል እንዳልተተገበረ ከመግለጹም በላይ በምርጫ ሒደቱ ላይ የተሳተፉ የቦርድ አባላት ስምንት መሆናቸው ቢገለጽም ፊርማቸውን ያኖሩት አምስት ብቻ መሆናቸው፣ የቦርዱ ሥራ አስፈጻሚና ሊቀመንበሩ በሒደቱ አለመሳተፋቸው፣ ቃለ ጉባዔውም በማን እንደተያዘ አለመታወቁና መሰል ክፍተቶችን በማውሳት የአዲሱን የቦርድ ሊቀመንበርነት እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡

የቦርዱ አስፈጻሚ አባል መሆናቸውን ጠቅሰውና ፈርመው ለኤጀንሲው ምላሽ በሰጡበት ደብዳቤ (ዶ/ር) አብዱልዋሀብ አደም ኢብራሂም ፣ ስድስት ዋና ዋና የሕግ ክፍተቶች በኤጀንሲው መፈጸማቸውን በመግለጽና አንቀጾችን በማጣቀስ የቦርድ አባላቱ ያካሄዱት ምርጫ ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት እንዳልተፈጸመበት ተከራክረዋል፡፡

እንዲያውም ኤጀንሲው ያላግባብ ሥልጣኑን በመጠቀም ጫና ማሳደሩንና አቶ ኢየሱስ ወርቅን ዳግም ወደ ኃላፊነት ለማምጣት ጣልቃ መግባቱን እና ጫና አሳድሯል ሲሉ ከሰዋል ክርክሩ ይህን የሚመስል ገጽታ ይላበስ እንጂ፣ ውስጥ ውስጡን ግን የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግባቸው ከቀረቡት ፕሮጀክቶችና ውድቅ ከተደረጉት ጋር እንደሚያያዝ አቶ ኢየሱስ ወርቅ አስታውቀዋል፡፡

በስም ያልተጠቀሱ የቦርድ አባላት የቦርዱ የሥነ ምግባር ደንብ የሚከለክለውን የጥቅም ግጭት ድንጋጌ በግልጽ በመተላለፍ የሥነ ምግባር ጥሰት መፈጸማቸው እንደተደረሰበት የተናገሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ የሥጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦች የተሳተፉበትና አንድ የቦርድ አመራር አባልም ድርጅታቸው የተወከለበትን ፕሮጀክት በማቅረብ ጭምር አብረው ለግምገማ መቀመጣቸው እንደተረጋገጠ በመግለጽ፣ እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች ቦርዱን እንደ ተፈታተኑትና እሳቸውንም ለመልቀቅ እንዳነሳሳቸው አስታውቀዋል ሲል ሪፖርተር ዘግቧል፡፡