አባይ ሚዲያ ግንቦት 11፤2012

ከቀናት በፊት መድረክ ስም ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት የተላከው ሰነድ ኢሶዴፓን እንደማይመለከተው የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አስታውቀው ነበር፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ከአባይ ሚዲያ ጋር ባድረጉት ቆይታ የመድረክ አባል የሆኑት ሶስት ድርጅቶች ምናልባትም በኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር  መረራ ጉዲና  ጫና በሰነዱ ላይ ሳይስማሙ እንዳልቀሩና በቀጣይ ከኦፌኮ ጋር ለመስራት እንደሚቸገሩ እንዲሁም የጥምረቱን ማዕከላዊ ኮሚቴ መጥራትና መነጋገር ግድ እንደሚል ነግረውናል፡፡

ኦፌኮ ከመድረክ ጋር አጋር ሆኖ እያለ በተለያዩ  ሰባት የፖለቲካ ፓረቲዎች በአቋቋሙት ትብብር ውስጥ መግባቱን የገለጹት ፕ/ር በየነ አሁን ደግሞ በመድረክ ስም ሰነድ ማዘጋጀቱ ተገቢ አለመሆኑን  አስረድተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአንድ በኩል በመድረክ ተጣማሪ ፓርቲዎች መካከል መከፋፈል ተፈጥሯል የሚሉ ድምጾች እየተሰሙ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ የሁለቱ ፕሮፌሰሮች መረራ ጉዲናና በየነ ጴጥሮስ ግላዊ ውዝግብ ነው የሚሉ አልጠፉም፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ አባይ ሚዲያ ያነጋገራቸው ሊቀመንበሩ ፕ/ር መረራ ጉዲና መንግስት ያቀረበውን አማራጭ እንድንቀበል አጋራቸው ጭምር ግፊት ማድረግ እንደሚፈልጉ አመልክተው የተፈጠረው ልዩነት ከግለሰባዊነት የተሻገረ ድርጅታዊ ምልክታ የለውም ሲሉም መልስ ሰጥተዋል።