አባይ ሚዲያ ግንቦት 11፤2012

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባወጣው መግለጫ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብሏል የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ መግለጫውን አስመልክተው እንደተናገሩት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ትጥቅ ያልፈቱ አካላት መኖራቸውን በማንሳት እነዚህ አካላት ባለፉት ወራት በዜጎች ላይ በተለይም ደግሞ በተመረጡ የመንግስት ሰራተኞች እና አመራሮች እንዲሁም ባለሀብቶች ላይ እስከ ግድያ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንደሚያደርሱ አንስተዋል አያይዘውም የንብረት ዝርፊያና ሰዎችን አግቶ ገንዘብ የመጠየቅ አዝማሚያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ሁኔታዎች ለመቆጣጠር ሲባል የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እርምጃዎችን እንደሚወስዱና እነዚህ ሀይል የተቀላቀለባቸው እርምጃዎች የዜጎችን ደህንነት ቅድሚያ ያልሰጡ በመሆናቸው ዜጎች በሁለት ወገን በሚደርስባው ችግርና ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን በማንሳት መንግስት ህግን በሚያስከብርበት ግዜ የሰብአዊ መብትን ባከበረ መልኩ መሆን እንዳለበት አቶ ቢኒያም አሳስበዋል በእርግጥ ኢሰመጉ በአንድ ሀገር ውስጥ ከመንግስት ውጪ ሌላ የታጠቀ ሀይል መኖር የለበትም ብሎ በጽኑ እንደሚያምን የገለጹት ዳይሬክተሩ የታጠቁ ሀይሎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱና ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ አካላት ትጥቃቸውን በመፍታት ወደሰላማዊ ትግል ለመግባት የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች መንግስት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመልስላቸው አሳስቧል በተጨማሪም መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ሀይሎች እያንዳንዱን ነገር ለማስፈጸም ሀይልንና ጉልበትን እንደሚጠቀሙ በማስታወስ የጸጥታ ሀይሎች የሚወስዷቸውን እርምጃዎች የሰብአዊ መብትን ባማከለና ባስቀደመ መልኩ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ፡፡

ጉባኤው አክሎም መንግስት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ተከላክሎ ዜጎች በሀገራቸው በሰላም ወደፈለጉበት የመንቀሳቀስ ነጻነታቸውን እንዲያስከብር አበክሮ አሳስቧል ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ሶሰት ሰዎች ተገድለዋል የሚል ጥቆማ ደርሶት እየተከታተለ መሆኑን የሰብአዊ መበት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በተለይም ከትላንት በስቲያ በመቀሌ ከተማ ርቀትን ለማስጠበቅ በሚል በጸጥታ ሀይሎች የተገደለውን ወጣት ጉዳይ እያጣራሁት ነው ብሏል፡፡
ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከዚህ በፊት በመቀሌ አንድ ወጣት ክልከላውን ተላልፈሃል በሚል በተፈጠረ ግጭት፤ በጸጥታ አስከባሪ አካል ግድያ እንደተፈጸመበት አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡን በማስተማርና ህግ በማስከበር ስራ ላይ የነበረ ጸጥታ አስከባሪ፤ በአዲስ አበባ በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቃት ደርሶበት ህይወቱ ማለፉን ተናግረዋል ይህ የሚያሳየው አዋጁን የማስከበሩ ስራ አስቸጋሪ መሆኑንና በሁለቱም ወገኖች በኩል ችግር መኖሩን ነው ይላሉ ዶ/ር ዳንኤል ባሁኑ ሰዓት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ክልከላ ለማህበረሰቡ ጤና መጠበቅ ቢሆንም፤ በጸጥታ አካሉ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች ግን በየትኛውም ሁኔታ ሊጣሱና ሊገደቡ የማይገባቸውን ሰብአዊ መብቶች የሚጥሱ መሆን እንደሌለባቸው ዶ/ር ዳንኤል አሳስበዋል፡፡