አባይ ሚዲያ ግንቦት 11፤2012

በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3,271 የላብራቶሪ ምርመራ የኮሮና ቫይረስ በአስራ አራት ሰዎች ላይ መገኘቱን ተከትሎ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 365 ደርሷል ቫይረሱ የተገኘባቸው 11 ወንድ እና 3 ሴት በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ከ9 እስከ 68 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የጤና ሚኒሰተሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አረጋግጠዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሊያ ማብራሪያ ቫይረሱ የተገኘባቸው 9 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ 1 ሰው የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ፣ 7 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 1 ሰው የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌለው ሰው ተገኝቷል፡፡

በተጨማሪም ከትግራይ ክልልና ከኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ አንድ አንድ ሰው የተገኘ ሲሆን ቀሪዎቹ  3 ሰዎች ደግሞ ከሶማሌ ክልል (ጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ) የተገኙ ናቸው በአጠቃላይ የዕለቱ ታማሚዎች ሁኔታ ሲታይ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው – 6፤ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው – 7 እንዲሁም የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌለው 1 ሰው ተመዝግቧል፡፡

የጤና ሚኒስተር መረጃ አክሎም 3 ከሶማሌ ክልልና 1 ከአፋር ክልል በአጠቃላይ  4 ሰዎች   ከበሽታው ያገገሙ ማገገማቸውን ተከትሎ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር አንድ መቶ ሃያ ደርሷል ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተጨማሪም በሰጡት ማብራሪያ በትላንትናው ዕለት (ግንቦት 10/2012 ዓ/ም) በወጣው መግለጫ ላይ ከአማራ ክልል (ሰሜን ሸዋ ዞን ፣ አጣየ ከተማ ለይቶ ማቆያ) ቫይረሱ በምርመራ የተገኘበት ተብሎ የተገለፀው በግንቦት 9 ቀን በወጣው መግለጫ ላይ ተጠቅሶ የነበረ መሆኑን እና በትላትናው ዕለት በድጋሚ ሪፖርት የተደረገ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በትላንትናው ዕለት ቫይረሱ በምርመራው የተገኝባቸው ሰዎች ቁጥር 34 መሆኑን ከይቅርታ ጋር ገልጸዋል ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፋር ክልል በአራት የለይቶ ማሰንበቻ ጣቢያዎች 486 ሰዎች ተለይተው ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሆነ ታውቋል በክልሉ በተለያየ አቅጣጫ በእግራቸው ጭምር ተጉዘው ድንበር አሳብረው የሚገቡ ስደተኞች በርካቶች ሲሆኑ በቀን በአማካኝ እስከ 350 ስደተኞች ከየመን እንዲሁም ከጅቡቲ በግመልና በእግር ተጉዘው በህገወጥ መንገድ በኬላዎቹ ያልፋሉ ተብሏል፡፡

የአፋር ክልል የወንጀል መከላከል ኮሚሽነሩንና የድንበር ጉዳዮች ሀላፊ ኮሚሽነር አህመድ አሪፍ እንዳሉት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስደተኞቹ ከማህበረሰቡ ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት በማቆያዎች ይሰነብታሉ የአፋር ሕዝብ ባህላዊ ዘዴዎችን ጭምር በመጠቀም የሳር ጎጆዎችን ቀልሶ ስደተኞቹን ለብቻቸው እያሰነበተ መሆኑንም ኮሚሽነር አህመድ ጠቅሰዋል፡፡