አባይ ሚዲያ ግንቦት 12፤2012

ትግራይ ክልል ወረዳ ለመሆን ያወጣውን መስፈርት አሟልተው ማዕከላቸውን ደንጎላት በማድረግ የመንግስት አገልግሎት በቅርበት ለማግኘት ያቀረቡት ጥያቄ እስካሁን አለመመለሱ አሳስቦናል ያሉ የደንጎላትና አካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ገልጸዋል በትግራይ ክልል ደቡብ ምስራቃዊ ዞን የደንጎላትና አካባቢው ህዝብ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸውን በማስታወስ፤ ቀበሌዎቹ በምክር ቤት ተሰብስበው ማዕከል እንዲሆን የወሰኑት እስካሁን ሳይተገበር መዘግየቱ ትክክል እንዳልሆነ አመልክተዋል።

ወረዳ መሆን ትክክለኛ እና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በመሆኑ ምላሽ እንዲያገኝ የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ አሁን ወደየትኛው ወረዳ እንደሚጠቃለሉ እንደማያውቁ፣ መንግስታዊ ግንኙነት መቋረጡን እና የመገለል ስሜት እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል በደቡብ ምስራቃዊ ዞንና ወረዳ አስተዳደር የሚደረገው የተቀናጀ መንግስታዊና የፓርቲ አፈና እና እስር እንዲቆምም ጠይቀዋል።

የትግራይ አክቲቪስቶችና ሚዲያ፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት በተለይ ከክልሉ ውጭ የሆነ ነገር ሲፈጠር የሚጮኹ፤ በክልሉ ውስጥ እንዲህ አይነት የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጠር ዝምታ የሚመርጡና የህዝባቸው ድምጽ የማያሰሙ ሆነዋል ብለዋል ወረዳ ለመሆን ላቀረቡት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ እንዲሰጠው ሊያግዙ እንደሚገባም ነው የተናገሩት። ካድሬዎች እንደሚያወሩት ጥያቄያቸው ሌላ ተልዕኮ ያነገበ ሳይሆን የሕዝብ ትክክለኛ ጥያቄና የመልማት ፍላጎት መሆኑን አመልክተዋል።

ከመቀሌ በስተደቡብ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው ደንጎላት ተገኝተው እውነታውን ከህዝቡ ጠይቀው ሊረዱ ይገባል እንጂ የአፈናው አካል መሆን እንደሌለባቸው፣ በተሳሳተ መንገድ ከመጓዝ ተቆጥበው ወደሕዝቡ ቀርበው በማጣራት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ጠይቀዋል የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ፤በበኩላቸው  የወረዳ ማዕከል የት ይሁን? የሚል ጥያቄ ተመልሷል ሲሉ ተናግረዋል።

ወረዳው ውስጥ ማዕከል የት ይሁን የሚለውን የሚወስነው የአካባቢው ሕዝብ እንጂ ክልል አይደለም ፤ የወረዳ ማዕከልነት የሁሉም ቀበሌ ነዋሪ በተወከሉበት ስለሆነ ክልል የሚወስነው ነገር እንደሌለ አክለዋል የህንጣሎ ወጀራት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ግርማይ፤ ወረዳ ለመሆን የተቀመጠውን መስፈርት ባለማሟላታቸው በቀጣይ የሚታይ ሆኖ አሁን አምደወያኔ ቀበሌ ሆነው እንዲቀጥሉ መወሰኑን ተቅሰው፤ የክልሉ ምክር ቤት ባወጣው መስፈርት መሰረት በቀጣይ ወደሳምረ ተካትተው እንዲተዳደሩ መደረጉንም ያክላሉ።

በተያያዘ ዜና ”ወረዳችን ይመለሰ” በሚል በሽሬ የማይ ሓንስ ነዋሪዎች በክልሉ መንግስት ላይ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል ህዝቡ ተቆጥቶ በአደባባይ ሰልፍ ወጥቷል፣ የትህነግ ልዩ ሃይሎች ተርበድብደዋል፣ ህዝባዊ ተቃውሞውም ዛሬ 5ኛ ቀኑን ባስቆጠረው ተቃውሞ ህዝቡ በአደባባይ ሰልፍ መውጣቱና መንገድ ዘግቶ እንደሚገኝ ታውቋል መንገዱ መዘጋቱን ተከትሎ  ከባድ ጭነት መኪናዎች መንገድ መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ከአካባቢው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡