አባይ ሚዲያ ግንቦት 12፤2012

በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት 3460 ሰዎች ተመርምረው 24 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም በየዕለቱ በጋራ በሚያወጡት መግለጫ በ69ኛው ሪፖርት አረጋግጠዋል በዚህም በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሮና ቫይረስ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 389 እንዲደርስ ሆኗል ዛሬ ከተያዙት 24 ሰዎች መካከል 18 ወንዶች ሲሆኑ የተቀሩት 6 ሴቶች ናቸው በዜግነት ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ተነግሯል።

9 ከአዲስ አበባ፣ 8 ሰዎች ከአማራ ክልል እንዲሁም 7 ሰዎች ከትግራይ ክልል የተገኙ ሲሆኑ12 የውጭ ሃገር ጉዞ ታሪካ ያላቸው፤ 8 ደግሞ በሽታው ካለበት ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው 4 ሰዎች ግን የጉዞ ታሪክም ሆነ ንክኪ የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ባለፉት 24 ሰዓታት ከአማራ ክልል ከበሽታው ማገገማቸው ታውቆ ከሆስፒታል እንዲወጡ ተደርጓል ይህም ያገገሙ ሰዎችን ቁጥርን 122 አድርሶታል።

እስካሁን ኮሮና በኢትዮጵያ ያለው ስርጭት ሲታይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንዳስታወቁት በአዲስ አበባ ከተማ ልደታና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በቫይረሱ የተጠቁ በርካታ ሰዎች ተገኝቶባቸዋል በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከተያዙት 365 ሰዎች መካከል 63 በመቶ  ወይም 228 ሰዎች በርዕሰ መዲናዋ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሁሉም ክፍለ ከተሞች መገኘቱን ገልጸው፤ የቫይረሱ ስርጭት በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል በዚህም በከተማዋ በቫይረሱ ከተያዙ አጠቃላይ 228 ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በልደታ ክፍለ ከተማ ይገኛሉ ብለዋል በአጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች 56 ሰዎች ወይም 16 በመቶ የሚሆኑት የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ እንደሌላቸው ዶክተር ኤባ ተናግረዋል።

ከነዚህም 48 በመቶ የሚሆኑት አዲስ አበባ እንደሚገኙና ከነዚህም 93 በመቶው በልደታና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እንደሚገኙ አስረድተዋል ለአብነትም ከሰሞኑ በልደታ በተደረገው በአንድ አዛውንት ላይ በተገኘው የኮሮና ቫይረስ 67 ሰዎች ንክኪ ያላቸው ሰዎች መለየታቸውን ገልጸዋል በእኚህ አዛውንት ምከንያትም አራት የቅርብ ሰዎችና አንድ ጎረቤት መጠቃታቸውን ጠቁመዋል።

ከአዛውንቱ ጋር ንክኪ  ያላቸውንም 95 ሰዎች ምርመራ በማድረግ 27 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እንደተረጋገጠ ጠቁመዋል በሌላ በኩል በዚሁ ልደታ ክፍለ ከተማ በአንድ ጊዜያዊ ማረሚያ ቤት በድምሩ 66 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ተረጋግጧል ብለዋል ይህም ታራሚዎችንና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችን እንደሚያጠቃልል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ይህም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በድንገተኛ በተደረገ የናሙና ምርመራ መሆኑን ገልጸዋል በመቀጠልም አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመዲናዋ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት የሚታይበት ነው ብለዋል ኅብረተሰቡ ከባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ በሽታውን መከላከል እንደሚገባም ዶክተር ኤባ አሳስበዋል የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው ሰርግና ለቅሶ ለቫይረሱ ስርጭት ዋነኛ ናቸው ብለዋል በመሆኑም ኅብረተሰቡ እንዲህ ያሉ ማኅበራዊ ክንውኖችን ማስቀረት እንዳለበት አሳስበዋል።