አባይ ሚዲያ ግንቦት 12፤2012

ከሰሞኑ አባላቶቼና ደጋፊዎቼ ያለአግባብ እየታሰሩብኝ ነው ሲል ቅሬታ ሲያቀርብ የነበረው ኢዜማ ፓርቲ አሁን ደግሞ የፓርቲው አመራር ኳራንታይን በሚል ሰበብ ለሶስት ቀን በእስር ቆይተው መውጣታቸውን ለአባይ ሚዲያ ተናግረዋል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ የቤተሰብ ለቅሶ ለመድረስ ጎፋ ልዩ ስሙ ሰላም በር ወደ ሚባል አካባቢ በተጓዙበት ወቅት አብረዋቸው ከተጓዙት ሰዎች ተነጥለው እሳቸው ብቻ በታጠቁ ሃይሎች ይፈለጋሉ ተብለው እንደተወሰዱ ከአባይ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል፡፡

ለምን እንደተፈለጉና የእስር ማዘዣ ወረቀት አሳዩኝ ብለው ቢጠይቁም ታጣቂው ማዘዣ አልያዝኩም ስለሚፈለጉ ነው ተብለው ያለ እስር ማዘዣ መወሰዳቸውንም ጨምረው ገልጸውልናል አቶ ዳንኤል በሰላም በር በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በእስር እንዲቆዩ እንደተደረገና ቤቱም እባብና የተለያዩ ተዋህሲያን የሚገኙበት ከመሆኑም በላይ መፀዳጃ ቤት እንኳን አልነበረውም ሲሉ የነበረውን ሁኔታ በምሬት ተናግረዋል፡፡

ያጋጠማቸው እስር ኳራንታይን በሚል እንደ ሽፋን የተጠቀሙበት ነው የሚሉት አቶ ዳንኤል ከሁሉም ተሳፋሪዎችና ከሳቸው ጋር አብረው ለቅሶ ለመድረስ ወደ ሰላም በር ካቀኑት አራት የቤተሰቦቻቸው አባላት አንጻር በሙቀት መለኪያ ሲታዩ የጤናማ ሰው የሙቀት መጠን እንደነበራቸውም አስታውሰዋል በአካባቢው በፖለቲካ ተሳትፏቸው ስለሚታወቁ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ሆን ብለው በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ ያለ አግባብ ለእስር እንደዳረጓቸው ገልጸዋል በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተደረገ ርብርብ ከእስር ሊለቀቁ መቻላቸውን ነግረውናል፡፡