አባይ ሚዲያ ግንቦት 13፤2012

‹‹በቀን አንድ ዶላር›› በማዋጣት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ድጋፍ እንዲሰጡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አነሳሽነት የተመሠረተው የኢትየጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ፣ በቦርድ አመራሮች ውዝግብ የህልውና አደጋ ውስጥ መውደቁን ሪፖርተርን ዋቢ አድረገን እሁድ ዕለት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በቦርድ ዳይሬክተሮች የሚመራው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በአባላቱ መካከል ውዝግብ መነሳት የጀመረው ካሰባሰው የስድስት ሚሊዮን ዶላር ውስጥ አምስት ሚሊዮን ዶላር በመመደብ፣ ከ22 ፕሮጀክቶች ውስጥ ለአምስቱ ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት አድርጎ ነበር ሲል  ዘገባው አትቷል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ሒደት ውስጥ ተከሰቱ በተባሉ የሥነ ምግባርና ሌሎችም በርካታ ከአሠራር ያፈነገጡ ተግባራት ምክንያት፣ የተቋሙ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በመግለጽ ደብዳቤ እንደጻፉ ተገልጿል እንደ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ሁሉ የእሳቸው ምክትል የሆኑት ዶክተር ምሕረት ማንደፍሮ እና የቦርድ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ፍቅሬ ዘውዴም ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን  ዘገባው አካቶ ነበር፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ መልቀቂያ ካስገቡ በኋላ በአስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፣ በምትካቸው አሜሪካ የሚገኙትን አቶ ዮሐንስ አሰፋ በቦርድ ሊቀመንበርነት ተሹመዋል ምክትል የነበሩት ዶክተር ምሕረት  አቶ ኢየሱስ ወርቅን ለመተካት መወዳደራቸውን፣ ሆኖም አቶ ዮሐንስ በሙሉ ድምፅ በመመረጥ አዲሱ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የቦርድ ሊቀመንበር መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

ነገሮች በዚህ መስመር ሲጓዙ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ ካለው የኃላፊነት ድርሻ በሚመነጭ አግባብ በነገሩ ጣልቃ በመግባት የአቶ ዮሐንስ የቦርድ ሊቀመንበርነት ምርጫ፣ ተገቢውን የሕግ ሒደት ያልተከተለ ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል አቶ ኢየሱስ ወርቅ በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ቦርድ አሠራር ውስጥ የሚታዩ ግድፈቶችና ሕጋዊነት የጎደላቸው እንቅስቃሴዎችን ሊታገሱ ባለመቻላቸው መልቀቂያ ቢያስገቡም፣ ኤጀንሲው ጥያቄያቸውን ሳይቀበለው እንደቀረ ሪፖርተር በሰጡኝ ቃለ መጠይቅ ለማወቅ ችያለሁ ሲልም ዘግቦ ነበር፡፡

ነገር ግን በዛሬው ዕለት የዲያስፖራ ትረስት ፈንዱ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰበስበውን ገንዘብ አለአግባብ ጥቅም ላይ አውሏል በሚል በመገናኛ ብዙሃን የቀረበው የተሳሳተ ዘገባ እንዳሳዘነው አስታውቋል ትረስት ፈንዱ የፋይናንስ አሠራር እና ደንብ ያልተከተለ ምንም አይነት የገንዘብ አጠቃቀም አሁንም ሆነ ለወደፊቱ እንደማይኖር አረጋግጧል፡፡

ተቋሙ ከ25 ሺህ በላይ ለጋሾች 6.36 ሚሊዮን ዶላር ከሰበሰበው 1.173 ሚሊዮን ዶላር ለወረርሺኙ መከላከል የሚውሉ የህክምና ዕቃዎች ገዝቶ ወደ ሀገር ቤት መላኩን ጠቁሟል በዚህም መሰረት ተቋሙ የሚሰበስበውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል ብክነትንና ስርቆትን ለመከላከል የሚያስችል ስርአት መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡