አባይ ሚዲያ ግንቦት 16፤2012

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተቋቋመው መርማሪ ቦርድ ጋር፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ አለመግባባት መፈጠሩ ታወቋል በተወሰኑ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ከቀረበው ምክረ ሐሳብ በተጨማሪ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ሊታረሙ ይገባቸዋል የሚላቸውን ኢሰብዓዊ አያያዞች የተመለከቱ መግለጫዎችን ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ እያወጣ መሆኑ፣ በሚኒስትሮች ኮሚቴ ውስጥ የሚሳተፉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማሰከፋቱ ተነግሯል ።

አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነት ከተሰጣቸው ባለሥልጣናት በተጨማሪ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን በተለይም ኢሰብዓዊ አያያዞችን ለማስቀረት ትኩረት በማድረግ እንዲከታተል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም፣ በኮሚሽኑ ላይ ቅሬታውን እያሰማ ነው ተብሏል የመርማሪ ቦርዱ ቅሬታ መሠረቱ ከሚኒስትሮቹ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመከታተል ሥልጣን የመርማሪ ቦርዱ፣ እንጂ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አይደለም ሲል የሕግ ጥያቄ አንስቷል።

ከዚህም በተጨማሪ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባልና የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በቅርቡ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የወጡ መግለጫዎች አሳሳቢ ናቸው››ብለዋል ሌላዋ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባልና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ‹‹ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ተገቢነት የላቸውም፤ የመብት ጥሰት ገጥሟልና ዕርማት ይደረግበት ቢሆን ሥራው ስለሆነ ትክክል ነው፤ ነገር ግን ከመጀመርያው አንስቶ ሕጉን የመተቸትና የተወሰኑ አንቀጾች እንዲወጡ የሚጠይቁ ናቸው፤›› ብለዋል።

መብቶች የተገደቡት ሕዝብን ለመጠበቅ እንጂ ሌላ ዓላማ እንደሌለው የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ኮሚሽኑ ይኼንን የሚያደርገው ካለመረዳት ከሆነ መነጋገር እንደሚቻል ገልጸዋል የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ አዋጁ በሕዝብ ላይ የተጫነ ዕዳ ሳይሆን ሕይወትን ለመታደግ የወጣ እንደሆነ በመጠቆም፣ ‹‹በሆነ አመለካከትና ፍላጎት ውስጥ ተሠልፈን የምንሳሳብበት ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው አዋጅ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ሐሳብ ሲቀርብ አይቻልም ማለት ትክክል አይደለም ብለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነትና በመሠረታዊ ድንጋጌዎቹ ላይ ኮሚሽኑ ልዩነት እንደሌለው፣ ነገር ግን የተወሰኑ አንቀጾች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ቢሆን ሊገደቡ የማይገባቸው ስለሆነ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኮሚሽኑ አስተያየት መስጠቱን አስረድተዋል የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሥራ የማይተካና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ደግሞ፣ ክትትሉ የበለጠ የሚፈለግበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል በመሆኑም አሁን የተፈጠረው አለመግባባት ተፅዕኖ እንደማያሳድርባቸው የገለጹት  ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል ፣ ‹‹መስማት የሚፈልጉትን ሳይሆን መስማት የማይፈልጉትን እያቀረብን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል ዘገባው የሪፖርተር ነው፡፡