አባይ ሚዲያ ግንቦት 16፤2012

በኮሮና ወረርሽኝ  ምክንያት በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ መደበኛ ባልሆኑ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ከ9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የአለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል የአለም የምግብ ድርጅት ሪፖርት ይፋ ባደረገው ጥናት፤ በርካታ የእለት ገቢ የሚያስገኙ የግል የሥራ ዘርፎች በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ሳቢያ በትንሹ ለቀጣይ ሶስት ወራት ዝግ ሆነው ሊቆዩ በመቻላቸው ሚሊዮኖች የሰው እጅ ጠባቂ ይሆናሉ ብሏል፡፡

የኢፌዲሪ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽንን ሪፖርት የጠቀሰው ጥናቱ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ወደ 1.9 ሚሊዮን የሚደርሱ የእለት ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁሞ ከእነዚህ መካከል በቀጣዮች 3 ወራት 750 ሺህ ያህል ገቢ የሚያስገኙ ስራዎች ይቆማሉ ብሏል ይሄን ተከትሎም በከተሞች የሚኖሩ ከ9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቀጣይ ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

በአሁን ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዘጠኝ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በኮሮና ምክንያት ለምግብ እጥረት እስከ መጪው ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ ይህ አሃዝ ወደ 43 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ተመልክቷል የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ በኮሮና ስጋት ሳቢያ የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል ብሎ በሪፖርቱ ያካተታቸው የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ጅቡቲ ናቸው::

በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚገኙ 3.3 ሚሊዮን ስደተኞችም ለከፋ የምግብ እጥረት ይጋለጣሉ ያለው ሪፖርቱ፤ ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የምግብ እጥረት እንዳይፈጠር ከመኸር ምርት በተጨማሪ 40 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል እንደሚመረት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ገልጸው ነበር፡፡

50 ሚሊዮን ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት መጀመሩም ነው የተገለጸው አቶ ዑመር ሁሴን  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ ምርትና ምርታማነት እንዳይቀንስ ከመደበኛው የእርሻ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ምርት የሚጨምሩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑንም ገልጸው ነበር የግብርና ሚኒስቴር ይህን ይበል እንጂ ከዚህ ቀደም የዓለም ምግብ ድርጅት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የዓለም አገራት ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም።