አባይ ሚዲያ ግንቦት 17፤2012

ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እንደማታካሂድ ከታወቀ በኋላ ምርጫውን ለማራዘም የሚረዱ አራት አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች መቅረባቸውን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ባዘጋጃቸው መድረኮች የህግና የህገ መንግስት ምሁራን ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸውን ሃሳቦች ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጠውን አማራጭ የህገ መንግስት ትርጓሜ የሚለውን ሃሳብ ጨምሮ አራቱም የመፍትሄ ሃሳቦች ተቀባይነት ስለሌላቸው መፍትሄው ፖለቲካዊ ነው የሚሉም አሉ ከዚህ ሁሉ ሁነት ባሻገር ግን ተደጋግሞ የሚነሳው  የህገ መንግስት ቀውስ የሚል ሃሳብ መሆኑ ሲደመጥ ቆይቷል፡፡

የህገ መንግስትና የሰብአዊ መብት ተመራማሪው ዶክተር ዘመላክ አይተነው የህገ መንግስት ቀውስ ማለት ፖለቲካዊና ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ላይ የሚነሱ ችግሮችም ሆኑ መልካም ነገሮች ጥያቄ ሊያስነሱ ስለሚችሉና ለጥያቄዎቹ ደግሞ መልስ ሊሰጥ ካልቻለ ህገ መንግስታዊ ቀውስ ተፈጥሯል ማለት እንችላለን ይላሉ፡፡

አሁን ባለው ሃገራዊ ሁኔታ ደግሞ ህገ መንግስቱ ቀውስ ውስጥ ገብቷል ብዬ አላምንም ፤ይልቁንስ ህገ መንግስቱ በሚገባ መፈተሽ አለበት ብለዋል የህገ መንግስት ትርጓሜ በራሱ የሚቆም ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁና ምርጫው ከተያዘለት የጊዜ ሰለዳ በመገፋቱ የመጣውን የህገ መንግስት ብዥታ እንዴት እንፍታው በሚል የተፈጠረ ጥያቄ እንደሆነ ዶክተር ዘመላክ የገልጻሉ፡፡

ሌላኛው የህገ መንግስትና የሰብአዊ መብት ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን አየለ በበኩላቸው የህገ መንግስት ቀውስ የሚከሰተው በህገ መንግስት ውስጥ በታቀፉ የህገ መንግስት አካላት መካከል በሚፈጠር ሽኩቻ አለመግባባት ሲፈጠርና ሊፈታ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ሲደርስ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ይህም ማለት በህግ አስፈጻሚውና በህግ ተርጓሚው መካከል ልዩነት ቢነሳና የህግ ተርጓሚው  አካል ውሳኔ አስተላልፎ  የህግ አስፈጻሚው አካል ያንን ባይቀበል የህገ መንግስት ቀውስ ተብሎ ሊጠራ ይችላል ይላሉ ሌላው ደግሞ ይላሉ ዶክተር ሰለሞን ምርጫን የሚያስፈጽመው አካል ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ የምርጫ ሂደቱ ችግር የሚኖረው አሊያም የምርጫ ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር ከሆነ የህገ መንግስት ቀውስ መገለጫ ይሆናል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ በሃገራችን ባለው ወቅታው ሁኔታ ስላልተስተዋለ የህገ መንግስት ቀውስ ተፈጥሯል ለማለት እንደማይቻል አስረድተዋል ዶክተር ሰለሞን ለሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች ማጣቀሻቸው ህገ መንግስት ስለሆነ በምንም ዓይነት ስምምነት ላይ የተመሰረተ ውጤት የትኛውንም የህገ መንግስት አንቀጽ፣የህገ መንግስት መርሆዎችና መዋቅር የሚያናጋ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡