አባይ ሚዲያ ግንቦት 18፤2012

የጤና ሚንስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፤ ባለፉት 24 ሰዓት ለ3410 ሰዎች ምርመራ ተካሂዶ 29 ወንዶችና 17 ሴቶች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ከእነዚህ መካከል 8ቱ የሚታወቅ የጉዞ ታሪክም ሆነ ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የላቸውም ተብሏል።

ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋጋጡ ሰዎችን ቁጥር ወደ 701 ከፍ አድርጎታል ኢትዮጵያ ባለፉት ቀናት ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሪፖርት ስታደርግ ነበር በተጓዳኝ ህመም ምክንያት በጽኑ ህክምና ላይ የነበረች እና በትላንትናዉ እለት ኮሮናቫይረስ የተገኘባት እና በተጓዳኝ ህመም የህክምና ድጋፍ ሲደረግላት የነበረች የ32 ወጣት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ኢትዮጲያዊት ትናንት ለሊት ሕይወቷ አልፏል፡፡

በዚህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ስድስት ደርሷል በኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥርም 87,264 ደርሷል ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት የኮሮና ቫይረስ አለባቸው ተብለው ሪፖርት ከተደረጉ ሰዎች መካከል ከአንደኛው ጋር ንክኪ አለን ያሉ 40 ያህል ሰዎች በጳውሎስ ሆስፒታል ደጃፍ ተሰልፈው መርምሩን እያሉ አቤቱታ እያሰሙ መሆኑን ሸገር ዘግቧል፡፡

ከኳስ ሜዳ አካባቢ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ንክኪ አለን ያሉ 40 ያህል ሰዎች በጳውሎስ ሆስፒታል ተገኝተው መርምሩን ቢሉም ሰሚ እንዳላገኙ ተናግረዋል ሰዎቹ የኢድ አልፈጥር ምሽት በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠው ልጅ ጋር አብረው ያመሹ ባለፉት ቀናትም የቅርብ ንኪክ ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የጳውሎስ ሆስፒታል በበኩሉ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ የሚታከሙትንና አስታማሚዎቸን በኮሮና ቫይረስ ስጠረጥራቸው ምርመራ አደርጋለው ከዛ ባሻገር ግን ራሱን ራሱን የጠረጠረን ሁሉ ለመርመር ሀላፊነት አልተሰጠኝም ብሏል በመጨረሻ ግን ሆስፒታሉ ለዛሬ 40ዎቹን ሰዎች እመረምራለሁ ለወደፊቱ ግን እንዲህ ያለ ነገር የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀላፊነት ስለሆነ ወደእኔ አትምጡ የሚል መልዕክት አስተላልፏል የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን የመለየት ሀላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መሆኑ ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል ታዲያ እነዚህን ሰዎች እንዴት ዘነጋቸው የሚለውን ለመጠየቅ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን ሸገር በዘገባው ጠቅሷል፡፡