አባይ ሚዲያ ግንቦት 20፤2012

በሊባኖስ መዲና ቤሩት ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላለፉት ሰባት ወራት ካለ ስራ መቀመጣቸውንና ከባድ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ከሳምንታት በፊት ዘግበን ነበር ስደተኞቹ በወቅቱም በሁኔታው ተስፋ ቆርጠው ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በኢትዮጵያ ቆንስላ በኩል የተጠየቁትን 550 ዶላር ከፍለው የተወሰኑት ሃገራቸው መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ ተራቸውን እየጠበቁ ባለበት ሁኔታ ኮሮና ቫይረስ በመከሰቱ ወደ ኢትዮጲያ የመመለሻቸው ነገር እየራቀባቸው መምጣቱን መግለጻቸውን መዘገባችንም አይዘነጋም ስደተኞቹ ባጋጠማቸው የገንዘብ ችግር ምክንያት ከ80 በላይ ልጆች አእምሮ በሽተኛ ሆነው ቆንስላው ውስጥ ሲኖሩ ወደ 100 የሚጠጉ ልጆች ደግሞ ህይወታቸው አልፎ አስከሬናቸው ማድረቂያ ውስጥ እንዳለም በወቅቱ ገልፀው ነበር፡፡

እነዚህ ዜጎችም በተደጋጋሚ ወደ አገራችን መልሱን የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተው የኢትዮጵያ መንግስትም ከሊባኖስ አቻው ጋር ባደረገው ውይይት ዜጎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስራ ሲሰራ ቆይቷል በወቅቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ቃል አቀባይ አምሳሉ ትዕዛዙ በቅርቡ ከሊባኖስ ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሚፈልጉ 624 ኢትዮጵያውያን በጥቂት ቀናት አዲስ አበባ እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልጸው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እየተከታተሉት መሆኑንም አቶ አምሳሉ ገልጸዋል በዛሬው ዕለትም በመጀመሪያው ዙር ዛሬ ጧት በዲፖርቴሽን ማዕከልና በእስር ቤቶች የነበሩ ዜጎች፣ በኮሙኒቲ እና በካሪታስ መጠለያዎች የነበሩ እንዲሁም ሌሎች ወደ አገራቸው ለመጓዝ ሲጠባበቁ የነበሩ በአጠቃላይ 337 ዜጎች ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።

የእነዚህ ዜጎች ሙሉ የትራንስፖርት ወጪያቸውን በኢትዮጵያ መንግስት በመሸፈን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል በምዝገባ ወደ አገር ቤት ለመጓዘ ለቀራማ እና ለትራንስፖርት ወጭዎች የሚሆን 550 ዶላር ከፍለው የነበሩ ዜጎቻችንም ሙሉ ገንዘባቸው 550 ዶላር ተመልሶላቸው ወደ አገር ቤት እንዲጓዙ መደረጉንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

እነዚህ ዜጎችም የኮቪድ19 ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅተው እንዲሄዱ በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ማመቻቸቱን አስታውቋል ከሊባኖስ የተመለሱ ዜጎችም ወደየቤተሰቦቻቸው ከመቀላቀላቸው በፊት በቀጥታ ወደ ተዘጋጀላቸው ለይቶ ማቆያዎች ይሄዳሉ በቀጣይም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይገባሉ ተብሏል።