አባይ ሚዲያ ግንቦት 22፤2012

የመብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ባለፈው የምዕራባውያን ዓመት ልዩ ልዩ መንግስታዊ የፀጥታ ኃይሎች እና ከእነርሱ ጋር በትብብር የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኢመደበኛ ቡድኖች አሰቃቂ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ሲል ወንጅሏል።

አምነስቲ ትናንት ይፋ ባደረገው የሰባ ሁለት ገፅ ጥናታዊ ዘገባው ለአንድ ዓመት ያህል በሁለቱ ክልሎች ባደረግኩት ምርመራ በኦሮሚያ ምስራቅ እና ምዕራብ ጉጂ እንዲሁም በአማራ ምዕራብ እና መካከለኛ ጎንደር ዞኖች የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ፖሊስ፣ የየአጥቢያ ባለስልጣናት እና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው የወጣት ቡድኖች አባላት በመብት ጥሰቶቹ ተሳትፈዋል ማለቱን ዘግበን ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የኦሮሚያ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ አምነስቲ  ከኒዮሊበራሊስት ተላላኪነት ወደ አብዮታዊ ድሞክራትነት አቋሙን ቀይሯል ሲሉ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ወርፈዋል ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰበአዊ መብቶች መጣሳቸዉ ባይካድም ህግን ከማስከበር አንፃር በመንግስት በኩል  ለተፈጠሩ ውስንነቶችና የወንጀሉ ድርጊቶች ዋና ተዋናይ ወያኔ ነበር ብለዋል።

አቶ ታዬ ወያኔ ወንጀሉን ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ ጀምሮ የብሔርና የሀይማኖት ግጭት ቀስቅሶ ህይወት እና ንብረት በማጥፋት እንደቀጠለ ይናገራሉ ተማሪዎችን እርስ በእርስ እስከማባላት የደረሰው ወያኔ ዋናዉ ግቡ የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ መድገም እንደሆነ ይታወቃል ሲሉ በጽሁፋቸው አመልክተዋል።

አቶ ታዬ አክለውም ለዓላማዉ ስኬት በርካታ ድራማዎችን የሰራ ሲሆን ጫወታዉን ደግሞ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች መሀከል በመከወን በሁለቱም ክልሎች ፅንፈኝነት እንዲነግስ ከማድረግ በተጨማሪ ለጫወታዉ ድምቀት ኦነግ-ሸኔን ወይም ጀዋርን እና አብን ወይም እስክንድርን አሰልጥኖ ያጫውታል ብለዋል፡፡

ወያኔ በዚህ መሀል ብዙ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ጥፋቶችን እያደረሰ የሚሰራቸዉን ወንጀሎች ደግሞ በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያ መንግስት ላይ ለማላከክ ጥሯል ይላሉ አቶ ታዬ አምነስቲ ደግሞ የወያኔን እና የባለሟሎቹን ፕሮፓጋንዳ “የዓመቱ ሪፖርት” ብሎ በመፃፍ  ከወያኔ የታረቀ ሲሆን፤  ወያኔም አምነስቲን ከኒዮሊብራሊስት ተላላኪነት ወደ ጓድ አብዮታዊ ዴሞክራትነት ቀይሯል፡፡

እዉነቱ ግን  መንግስት ሰብአዊ መብቶችን ለማስከር ከነውስንነቱ ብዙ ስራ አከናውኖ የወያኔን ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያ እንደ ሊብያ ወይም እንደሩዋንዳ እንዳትሆን በማድረጉ ሊወገዝ ሳይሆን ሊመሰገን ይገባል ብለዋል ይህ በእንዲህ እንዳለ የአምነስቲ መግለጫ ሚዛናዊነት የጎደለውና የተሳሳተ መሆኑን የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ገልጸዋል።

መግለጫው የአንድ ወገን መረጃን ብቻ በመያዝ ሚዛኑን ያልጠበቀና የተሳሳተ በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል ብለዋል ሪፖርቱ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበና በተለይ ነፍጥ ያነገቡ ታጣቂዎች በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብና የመንግሥት ኃይሎች ላይ የሚፈፅሙትን ወንጀል መካዱንም አብራርተዋል።