አባይ ሚዲያ ግንቦት 22፤2012

ኢትዮጵያ የምትሰራውን የህዳሴ ግድብን ሚስጥር በሚመለከት ከውጪ ሰላዮች ባልተናነሰ በሀገር ውስጥ በሚወሩና በሚነገሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ልታደርግ እንደሚገባ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና በሶማሊያ የቀድሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሽን ቡድን መሪ የነበሩት በተጨማሪም  የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፓርቲ (ኢዜማ) ጋር የተቀላቀለው ራእይ ፓርቲ መስራችና ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉት አቶ ተሻለ ሰብሮ መክረዋል፡፡

አቶ ተሻለ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው ሀይል ጋር ተያይዞ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ በቀጠናው የሚኖራትን ተደማጭነት የሚያሳድግ መሆኑንና የአካባቢያዊ ፖለቲካ ሀይል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል ግብጽ ይህንን ጠንቅቃ ስለምትረዳ የሚያሳስባት ኢትዮጵያ ስለምትገነባው የሀይል ማመንጫ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ግፋ ሲልም በአህጉሪቱ ላይ ያላትን የበላይነት ማስቀጠል የመፈለግም ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር ሆና እንድትቀጥልና ሁለንተናዊ እድገቷን እንድታፋጥን ግብጽም ሆነች ምእራባዊያኑ ፈጽሞ የሚፈልጉት ጉዳይ አለመሆኑንም አንስተዋል በእነዚህ ምክንያት ግብጽ ከውስጥ ያሉ ሀይሎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ተሰሚነትና የበላይነት ለማዳከም የማትተኛ በመሆኑ መንግስት ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በኢትዮ ሱዳን ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሽን ቡድን መሪ እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ተሸለ ሰብሮ የዚያድባሬ መንግስት ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ወዳጅ መስለውን አብረው የነበሩ ሰዎችና ቡድኖች በጎን ከወራሪው ሀይል ጋር ተሰልፈው ነበር ብለዋል ስለሆነም ዛሬም በውስጣችን ለእነርሱ የሚሰሩ ስለሚኖሩ ዙሪያችንን መመልከት አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች ከውስጥም ይሁን ከውጭ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች በራሱ ከፋፋይና አደገኛ ስለሚሆን ለመናገር ብቻ ባይናገሩ ይበጃል ያሉት አቶ ተሻለ ሀሳቦቹ የባንዳ ተልዕኮ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ በመግለጽ መንግስት ጥብቅ ክትትል አይለየው ብለዋል በመጨረሻም መንግስት አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በመጠበቅ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቧን ማጠናቀቅ እንድትችል ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚነሱባትን ደመኞቿን በደንብ መመልከት ስትችል ነው ሲሉ አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡