አባይ ሚዲያ ግንቦት 23፤2012

በዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ውስጥ የከረሙት ሶማሊያና ሶማሌላንድ ዳግመኛ ያገረሸ ቁርሾ ውስጥ የገቡት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጣለውን ማዕቀብ በመጣስ ግብፅ ለሞቃዲሾ መንግሥት የጦር መሣሪያ ዕርዳታ መስጠቷን የሚያመላክቱ መረጃዎች በመውጣታቸው ነው ከሶማሌላንድ መንግሥት አፈትልኮ የወጣ ደብዳቤ ከወራት በፊት በሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ተፈርሞ ለግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ፣ ርክክብ የተፈጸመባቸውን መሣሪያዎች ዝርዝር ያሳያል፡፡

የካቲት 21 ቀን 2012 ወይም እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 29 ቀን 2020 የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ሐሳን አሊ ሞሐመድ ለግብፅ መንግሥት በጻፉት ደብዳቤ፣ 50 አርፒጂ-7 ላውንቸሮች፣ 36 የአልሞ ተኳሽ ጠብመንጃዎች ከ1,000 ጥይቶች ጋር፣ እንዲሁም ሌሎች 13 ዓይነት በዝርዝር የጠቀሷቸው የጦር መሣሪያዎች እንደተረከቡ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም መሠረት ብዛታቸው 1,200 ክላሽኒኮቭ (ኤኬ47) ጠመንጃዎች፣ 25 ፒኬኤም መካከለኛ አውቶማቲክ መሣሪያ ከ700 ጥይቶች፣ 175 ፒኬኤም ቀላል አውቶማቲክ መሣሪያ ከ700 ጥይቶች፣ 50 አርፒጂ-7 ላውንቸሮች፣ 36 ባለ 12.7 ሚሊ ሜትር ደሸከ (ዶሽቃ) ከባድ አውቶማቲክ መሣሪያዎች፣ ስድስት ባለ 82 ሚሊ ሜትር ሞርታር ከ550 ተተኳሽ ጥይቶች ጋር፣ እንዲሁም 12 ባለ 60 ሚሊ ሜትር ከባድ ሞርታሮች ከ636 ሽጉጦች ጋር ግብፅ ለሶማሊያ መከላከያ ሠራዊት መለገሷን ከደብዳቤው ለመረዳት ተችሏል፡፡

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር የተደረገለት የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለአገሪቱ የፀጥታ ሥራ ብቻ እንደሚውል፣ በፍጹም ለሽያጭ ወይም ላልተፈቀደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እንደማይተላለፍ በመግለጽ ለግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር ጽፏል ይኼንን ተከትሎ የሶማሌላንድ መከላከያ ሚኒስትር አብዲቃኒ ሞሐሙድ አቲዬ በትዊተር ገጻቸው የአፍሪካ ኅብረትን፣ ተመድንና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሒን ጠቅሰው በጻፉት ማሳሰቢያ ግብፅና ሶማሊያን ኮንነዋል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት ለዓመታት ተጥሎበት የቆየውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ አለማክበሩን ያወሱት የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የግብፅ መንግሥትም በሶማሊያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ሆን ብሎ በመጣሱ እንቃወመዋለን፡፡ ይህ ድርጊት በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል ጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም በሚመለከት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠይቆ የሁለቱ አገሮች ጉዳይ በመሆኑ ምንም ዓይነት ምላሽ መስጠት እንደማይችል አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ይህን ይበል እንጂ፣ በቀጣናው የፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ የካበተ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙዎች ግን፣ መንግሥት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እያለዘበና ቸል እያለ የመጣውን የሁለትዮሽ የፀጥታ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥበትና ፖለቲካዊ አሠላለፎች መለወጣቸው የሰላምና መረጋጋት ችግሮች እንዳያስፋፋ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደርና ለመተናኮስ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም የሚሉት የዘርፉ ተንታኞች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ ትብብሮችን በመመሥረት ሰበብ ከደቡብ ሱዳን ጋር፣ አሁን ደግሞ ከሶማሊያ ጋር በግላጭ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ማድረጓ መልዕክት አለው ማለታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡