አባይ ሚዲያ ግንቦት 23፤2012

ከቀናት በፊት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልል ላይ ጥናት አድርጌ አወጣሁት ያለውን ሪፖርት የአማራ ክልል መንግስት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያቀረበው ሪፖርት ኢ-ምክንያታዊና ኢ-ፍትሐዊ ነው፡፡

መስከረምና ጥቅምት ወራት አካባቢዎች በጎንደርና አካባቢዋ ግጭቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ የግጭቱ መነሻም በጽንፈኝት በሚንቀሳቀስ ቡድን በተሠራ ሥራ መሆኑን አስታውሰዋል በግጭቱም ንጹኃን ሰዎችም የፀጥታ ኃይል አባላትም የሕይወትና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሀብትና ንብረት ወድሟል፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል፡፡

ይህን ጉዳይም ‘‘የክልሉ መንግሥት አውግዟል፤ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታትም ጥረት በማድረጉ ሰላማዊ መንገድ ፈጥሯል’’ ብለዋል ‘‘አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰው ልጅ መብት ሲጣስ የሚቆመውን ጥብቃና እንቀበላለን፤ ነገር ግን ከሰሞኑ በክልሉ ላይ ያወጣውን ሪፖርት አንቀበለውም’’ ብለዋል፡፡

የወጣው ሪፖርትም ለሰው ልጅ ተቆርቋሪና ሰበዓዊነትን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን ገልጸዋል ‘‘ሪፖርቱ አድሏዊነት ያለው፣ የተፈጸመን ድርጊት በሚገባ ያልገለፀ፣ ያልተነተነና በይፋ ያላወጣ ነው’’ ነው ያሉት ሃላፊው ሪፖርቱ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ላይ ብቻ ማተኮሩም ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሪፖርቱ ሲሠራ መሠረታዊ የሚባሉ የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የመንግሥት ተቋማት እንዳልተካተቱበትም ጠቁመዋል ከመንግሥት ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎች ተገቢው መረጃ ያልተሰበሰበና በተገቢው መንገድ ያልተነተነ መሆኑንም የሪፖር ጉድለት እንደሆኑ አስታውቀዋል አቶ ግዛቸው ‘‘ከሰላምና ደኅንነት ወሰድኩት የሚለውን መረጃም በአግባቡ ያልተካተተ በመሆኑ ሪፖርቱን ዕውቅና አንሰጠውም’’ ያሉም ሲሆን ሪፖርቱ የአንድን ወገን ብቻ ለማዳመጥና አንድን ወገን ብቻ የተጎዳ አስመስሎ የቀረበ እንደሆነ እንደተረዱ ገልጸው ‘‘የክልሉን መንግሥት ያላወያዬና መረጃ ያልወሰደ ሪፖርት ተገቢነት የለውም’’ ብለዋል፡፡

ሪፖርቱ የችግሩን ምንጭና መነሻ የሆነውን መንገድ አለማሳየቱም ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል ‘‘የነበረውን ችግር አማራ በቅማንት ላይ የዘመተ አስመስሎ ማውጣቱ በጋራ የኖሩ፣ እየኖሩ ያሉና ወደፊትም አብረው የሚኖሩ ወንድማማች ሕዝቦችን የሚያቃቅር ነው’’ ብለዋል ከምዕራብና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች 57 ሺህ የሚደርሱ ወገኖች እንደተፈናቀሉ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ተፈናቃዩ የሁለቱም ወገን ሆነው ሳሉ ቅማንት ብቻ በተለዬ መንገድ እንደተፈናቀለ አድርጎ መቁጠሩም የሁለቱን ሕዝቦች አብሮነት ያላገናዘበ ለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

‘‘ሪፖርቱ ምክንያታዊ ያልሆነና ፍትሐዊነት የጎደለው ነው’’ ያሉት አቶ ግዛቸው የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ችግሩን ለመፍታት የሄዱበትን መንገድ ያልዳሰሰ ነውም ብለዋል ሪፖርቱ የችግር ፈጣሪዎችን ሚና ያልዳሰሰና ያልተቸ በመሆኑ ሚዛን የጎደለው ነውም ብለዋል የአማራ ክልል ሕዝቦች በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል ያሉት አቶ ግዛቸው ትክክለኛ የሰበዓዊ መብት ተሟጋች ከሆነ ይህን ሁሉ አካትቶ ማቅረብ ነበረበትም ብለዋል፡፡