አባይ ሚዲያ ግንቦት 24፤2012

የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ዕርስቱ ይርዳው በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ለይ እንዲሁም በደቡብ ክልል ፖለቲካ ዙሪያ ከአባይ ሚዲያ እንግዳችን ዝግጅት ጋር ቆይታ አድርገዋል አቶ ዕርስቱ በክልሉ ቀድሞ በነበረው አስተዳደር ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች ለውጡን ተከትሎ በመነሳታቸው ጥያቄዎቹ አቅጣጫቸውን ቀይረው ወደ ቁጣ በመግባት በርካታ ግጭቶች ፣የንብረት ውድመቶች ፣የሰው ህይወት ማለፍና መፈናቀሎች በክልሉ ሁሉም ቦታዎች ተከስተው ነበር ብለዋል፡፡

ይህም ችግር ብሄርን ከብሄር የለየ ሳይሆን የህዝቡ ስሜት ገንፍሎ በመውጣቱና የአመራሮቹ ችግሩን ለመቆጣጠር ያሳዩት ክፍተት ፤እንዲሁም ችግሩን ቀርቦ በውይይት መፍታት እየተቻለ ፤ቁርጠኛ አለመሆን ግጭቱ እንዲከሰት አድርጎታል ብለዋል አቶ ዕርስቱ በክልሉ ያሉ ሁሉም ዞኖች በምክር ቤታቸው የክልል ይሰጠን ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን መንግስትም ለነዚህ ሁሉ ዞኖች የክልልነት ጥያቄን መመለስ ስለማይችል ፤በፌደራል መንግስት ድጋፍ ከሁሉም ዞኖች ከተውጣጡ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ገለልተኛ የሆነ ከሁሉም አካባቢ የተውጣጡ ከሰማኒያ በላይ ህዝብን የወከሉ አካላት ቡድን የተደራጀ ሲሆን እነዚህ አካላት ህብረተሰቡን አነጋግረው መፍትሄ መሆን ያለባቸውን ነጥቦች ከሁሉም አካባቢ ነዋሪዎች ጋር በመወያየት መፍትሄ ለማምጣት እየሰራና ከህዝቡም አስተያየት ሰብስቦ መጨረሱን ገልጸዋል፡፡

ይህ የተቋቋመው ቡድን የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባና ፣የቀሪዎቹን ዞኖች አብሮ የመቀጠል ሂደት የሚያጠናክር እንዲሁም ጠቃሚ መፍትሄ የሚሰጥ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል አቶ ርስቱ በኔ በኩል የቀድሞው የደቡብ ክልል በነበረበት ይቀጥላል ማለት ባልችልም ፤ክልሉ ወደ ተለያዩ ዞኖች ቢከፋፈል እንኳን የኔና የስራ ባልደረቦቼ ሃላፊነት የሚሆነው በሰከነ መንገድ እንዲከናወን ሂደቱን ሰላማዊ ማድረግ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡