አባይ ሚዲያ ግንቦት 26፤2012

በአሜሪካና በዓለም ባንክ የታዛቢ/አደራዳሪነት ሚና በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል በታላቁ በህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተቋርጦ ሦስቱ አገሮች ዳግም ወደ ሦስትዮሽ ድርድር ውይይት ለመመለስ ፍላጎት ካሳዩ በኋላ፣ የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረት አደራዳሪ ለመሆን ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል።

በአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር ስማኤል ቼሩጊ ባለፈው ሳምንት ከአውሮፓ ኅብረት ምክትል ኮሚሽነርና የኅብረቱ የውጭ ግንኙነትና የደኅንነት ጉዳዮች ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሮሌ ጋር በህዳሴ ግድቡ ላይ ሦስቱ አገሮች ለማድረግ ስላሰቡት ድርድር፣ እንዲሁም ሁለቱ አኅጉሮች ስለሚኖራቸው ሚና  መወያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይኼንኑ የባለሥልጣናቱን ውይይት አስመልክቶ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ፣ በሦስቱ አገሮች መካከል ያለው ልዩነት ከዚህ በላይ መካረር እንደሌለበትና በፍጥነት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔ ሊፈለግ እንደሚገባ መወያየታቸውን  አትቷል በዚህ ረገድ ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉትን ውይይት የአውሮፓ ኅብረት ለመደገፍና የኅብረቱ የቴክኒክ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን በማካፈል እንዲያግዙ ከተፈለገም ኅብረቱ ዝግጁ መሆኑን እንደገለጹ መግለጫው ያስረዳል።

የግብፅ መንግሥት በበኩሉ የአፍሪካ ኅብረት እንዲያደራድር የቀረበውን ሐሳብ እንደማይቀበል መግለጹን  እየወጡ ያሉ መግለጫዎች ጠቁመዋል ግብፅ የአፍሪካ ኅብረትን አደራዳሪነት ላለመቀበል ስትል ከምታነሳቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በአዲስ አበባ መሆኑና ኅብረቱም የኢትዮጵያ ተፅዕኖ አለበት የሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የሚመጣ ውጤት የግብፅን ጥቅም የሚጎዳ ቢሆንና ግብፅ ውጤቱን ላለመቀበል ብትወስን የኅብረቱ አባል ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች በሙሉ እንደሚያቃርናት፣ ይህም አጠቃላይ የዲፕሎማሲ ኪሳራ እንደሚያደርስባት በመሥጋት የኅብረቱን የአደራዳሪነት ሚና ላለመቀበል አቋም መያዟን ምንጮች ያስረዳሉ።

የኅብረቱ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በተናጠል የአፍሪካ ኅብረት በአደራዳሪነት እንዲገባ ለግብፅ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ የግብፅ መንግሥት ሳይቀበለው መቅረቱን ጠቁመዋል ሌላኛው አማራጭ የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት በጋራ ሆነው እንዲያደራድሩ፣ በሁለቱ አኅጉራዊ ኅብረቶች በኩል ጥያቄ እየቀረበ ሲሆን፤ የግብፅ መንግሥት ይኼንንም ለመቀበል ዳተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በህዳሴ ግድቡ ላይ ከተሰማሩት ኩባንያዎች መካከል ዋነኞቹ የጀርመን፣ የፈረንሣይና የጣሊያን በመሆናቸው ኅብረቱ በገለልተኝነት ለማደረደር አይችልም የሚል ደካማ መከራከሪያ በግብፅ ባለሥልጣናት በኩል እየተራመደ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል ይህ ቢሆንም የግብፅ መንግሥት የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረቶች በጋራ የአደራዳሪነት ሚና እንዲይዙ የቀረበውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አለማድረጉን የጠቆሙት ምንጮች፣ ሐሳቡን በከፊል እንደምትቀበለው ነገር ግን ከሁለቱ ኅብረቶች በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥትም እንዲሳተፍ ጥያቄ እያቀረበች መሆኑን ገልጸዋል።