አባይ ሚዲያ ግንቦት 27፣ 2012

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በውስጡ ድብቅ እስር ቤት አለ መባሉን አስተባበለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ማቆያ መነሻ አድርጎ በአየር መንገዱ ላይ የሚናፈሰው ወሬ ሐሰት ነው ሲሉ የአየር መንገዱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የገበያ መምሪያ ኃላፊ ተናገሩ ከአፍሪካ አየር መንገዶች ቀዳሚና ስመጥር የሆነው በዚህ በአስቸጋሪ ጊዜ  እንኳን እጅ ያልሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በብርቱ እየደገፈ ቀዳሚውን የውጭ ምንዛሬ አምጪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚደነቀውን ያህል ስሙም በሌላ ይነሳል ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስር ቤት አለው የአየር መንገዱ ነው በተባለው እስር ቤትም የሰዎች ሰብአዊ መብት እንደሚጣስና ሌሎች ነገሮችም እንደሚደረጉ ሰሞኑን በተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገፆች ስሙ ተነስቷል በጉዳዩ ላይ ለሸገር ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የገበያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ወልደ ማርያም በአየር መንገዱ በድብቅ ሳይሆን በግልፅ የፖሊስ ማቆያ አለ፤ ይህም የወንጀል ተጠርጣሪዎች ወደ ዋናው ፖሊስ ጣቢያ እስከሚወሰዱ ድረስ ፖሊሶች እነሱን የሚያቆዩበት ነው ብለዋል፡፡

ይህም ማቆያ የአየር መንገዱ ሳይሆን የፖሊስ ነው ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል ኃላፊው አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሌላ ሀገር ለመብረርና ተወዳዳሪ ለመሆን የአየር መንገዱ መነሻ የሆነው ኤርፖርትና አጠቃላይ ወደቡ የተጠናከረ ፀጥታ እና ደህንነት አንደኛው መስፈርት ስለሆነ የማቆያው ቦታ አስፈልጓል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድብቅ እስር ቤት አለው በዚህም አየር መንገዱ ሰራተኞችን ይበድልበታል እንዲሁም ሰዎች ይደፈሩበታል መባሉን የተጠየቁት አቶ ኢሳያስ ይህ ባለማወቅ የሚወራና ፈፅሞ ስህተት ያሉ ሲሆን ማቆያውንም አየር መንገዱ እንደማያስተዳድረው ተናግረዋል ማቆያውም በሌሎች አለም አቀፍ አየር መንገዶች እንደሚገኘው አይነት መሆኑንም ገልፀዋል እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ ከለውጡ በኋላ በተለይም ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ የአየር መንገዱ ስም በሀሰት እንደሚነሳና በተለይም ከብሄር ጋር በተያያዘ ያልሆነ ስም እየተሰጠው ነው፡፡