አባይ ሚዲያ ግንቦት 27፣ 2012

በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 5141 የላብራቶሪ ምርመራ አንድ መቶ ሃምሳ  ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1,636 ደርሷል የኮሮና ቫይረስ በምርመራ ተገኝቶበት በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ህክምና ሲደርግለት የነበረ፣ ከዚህ ቀደም ተጓዳኝ ህመም ያለበት እና በፅኑ ህክምና ላይ የነበረ የ30 ዓመት ኢትዮጵያዊ በትላንትናው ዕለት ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

በዚህም በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር አስራ ስምንት ደርሷል በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት አራት ሰዎች ከአዲስ አበባ ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 250 ነው ይህ በእንዲህ እንዳለ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሦስት ወረዳዎች 17 ቀበሌዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር ከሱዳን ጋር የሚዋሰኑ በመሆኑና በየዕለቱም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበሩን በማቋረጥ ወደ ኢትዮጵያ በመግባታቸው ምክንያት አካባቢው ከኮሮና መስፋፋት ጋር በተያያዘ የስጋት ቀጠና ሆኗል።

በአካባቢው በለይቶ ማቆያ ማዕከል እጥረት እየተሰቃየን ነው ያሉት የመተማ ወረዳ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በቃሉ እውነቱ ናቸው አቶ በቃሉ ኮኪት ለይቶ ማቆያ ማዕከል ላይ ስፍራ በመጥፋቱ ብዙ ሰው ማስገባታቸውን  ተናግረዋል። ይህንንም ሲያብራሩ “የኮኪት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጀመሪያ ጥናት ተደርጎበት ስንሠራ ለ80 ሰዎች ብቻ ነው የሚሆነው ብንልም ስላልቻልን 400 ሰዎችን አስገባን።

መጀመሪያ ቀን 2 ሰዎች ፖዘቲቭ ሆኑ፤ በሚቀጥለው ጊዜ 8 ሰዎች [ቫይረሱ] ተገኝቶባቸዋል። ይህ ደግሞ መጨመሩ አይቀርም” ብለዋል በአካባቢው ከሱዳን ከ200 እስከ 300 የሚሆኑ ሰዎች በየዕለቱ ይገባሉ “በመተማ ዮሃንስ ብቻ ኳራንቲን ከተጀመረ በኋላ ከ1300 የሚበልጡ ሰዎች ሙቀት ለክተን መርምረን ወደ መኖሪያቸው ልከናል” ሲሉ ገልጸዋል ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ በሚረዝመው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ህጋዊ እና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚገባባቸው ብዙ በሮች መኖራቸው ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው “በደሎሎ፣ በቲያ፣ በቱመት እና በሌሎችም በሮች አንዴ ዘግተን ብንሰራ ጥሩ ነበር” ይላሉ አቶ በቃሉ።

እንደ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊው ከሆነ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ ብዙ መግቢያ ቦታዎች አሉ። መጀመሪያ በሽታውን ለመከላከል ከቋራ እስከ ምዕራብ አርማጭሆ ድረስ መስመሩ መዘጋት አለበት የሚሉት ኃላፊው፣ ከዚያም በዚህ ይውጡ በዚህ ይግቡ በማለት መለየት እና ከሱዳን የሚመጡትን ሰዎች ይዞ ማከም ይቻል ነበር ሲሉ ለበቢሲ ተናግረዋል ” ከዚያ ኳራንታይን በማመቻቸት ሰዎችን 14 ቀን አቆይቶ ናሙና በመውሰድ ቫይረሱ ያለባቸውን ማከም ሌሎችን ደግሞ ወደ ቀዬአቸው መላክ ነው ያለበት። በክፍል እና በቦታ ጥበት ምክንያት ግን አልሆነም ” ሲሉም ያስረዳሉ።