አባይ ሚዲያ ግንቦት 30፤2012

በኤካ ኮተቤ ለሕክምና የገቡ ታማሚዎች በበርካታ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለሆስፒታሉ ኃላፊዎች ለማሰማት ቢሞክሩም፣ ሰሚ እንዳላገኙና መፍትሔም የሚሰጣቸው እንደሌለ ተናግረዋል ከደቡብ ሱዳን መጥታ በሆስፒታሉ ሕክምና እየተከታተለች የምትገኝ አንዲት ታካሚ፣ በሆስፒታሉም ሆነ ወደ ሆስፒታል ከመወሰዷ አስቀድሞ ስለነበረው መጉላላትና ፈር ያልያዘ አሠራር አምርራ ትናገራለች ታካሚዋ ከደቡብ ሱዳን በግንቦት ወር መጥታ በሳፋየር አዲስ ሆቴል ቆይታ ለምርመራ የሚሆን ናሙና ከሰጠች በኋላ፣ በተደጋጋሚ እየተደወለላት ተጓዳኝ በሽታ ያለባት እንደሆነ ትጠየቅ እንደነበር ትናገራለች፡፡

‹‹‹ከእስራኤል የመጣሽ እስራኤላዊት ነሽ አይደል?› እያሉ በተደጋጋሚ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ይሁንና እኔ ኢትዮጵያዊት ነኝ፣ ከእስራኤልም አልመጣሁም ብላቸውም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥያቄ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ አይደለም ብላቸውም የስልክ ቁጥርሽ ተመሳሳይ ነውና ስህተት ሊሆን አይችልም አሉኝ፡፡ ከሌላ ሰው ጋርም ንክኪ ኖሮኝ እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡ ከውጭ ከመጣሁ ጀምሮ ሆቴል እንደቆየሁና ከማንም ጋር እንዳልተገናኘሁ ተናገርኩ፡፡ ነገር ግን ጥያቄዎቻቸው ስህተት ይሆናሉ የሚል ጥርጣሬ ስለፈጠረብኝ በድጋሚ ናሙና ውሰዱና መርምሩኝ አልኳቸው፡፡ ነገር ግን በድጋሚ ናሙና ለመውሰድና ለመመርመር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ፡፡ ስለዚህ አሁን ቫይረሱ በርግጠኝነት ይኑርብኝ አይኑርብኝ አላውቅም፤›› ትላለች፡፡

ይኼ የመረጃ ልውውጥ ቢደረግም በነጋታው የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አንድ ከእስራኤል የመጣች እስራኤላዊት ቫይረሱ ተገኝቶባታል ተብሎ ሲገለጽ እንደሰማች፣ ይኼም ቤተሰቧን ግራ እንዳያጋባ ስትል እንዳስታወቀቻቸው ታስታውሳለች፡፡ ‹‹የእኔ ዕድሜና በመግለጫው የተገለጸው ዕድሜ ይለያያልም፤›› ብላለች ‹‹ሐኪሞች እየመጡ ስማችንንና የሚሰማን ሕመም ከመጠየቅ ውጪ ምንም ዓይነት ሕክምና አይደረግልንም፤›› ስትልም በሆስፒታሉ ያለውን ክትትል ትገልጻለች፡፡

ሌላው ሪፖርተር ያናገራቸው ታማሚ የፖሊስ ባልደረባ ከሥራ ባህርያቸው የተነሳ በግድ እንዲመረመሩ ተደርገው ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና ወደ ሕክምና እንደተወሰዱ በመግለጽ፣ ‹‹ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ዓርብ ዕለት አገግመሃል ተብዬ ያገገሙ ሰዎች ወደሚቆዩበት አራተኛ ፎቅ ተወሰድኩ ይላሉ የሚያስልም ሆነ ከተለመደው ውጪ ደጋግሞ የሚያስነጥስ አይታይም፡፡ ሐኪሞቹም ተሸፋፍነው መጥተው ስማችንን ብቻ ጠይቀውን ይሄዳሉ፤›› በማለት ያለውን ሁኔታ ይገልጻሉ፡፡

በአንድ ክፍል ከሰባት እስከ ስምንት ሰው መኖር ፤በውሃ የተሞላ የሽንት ቤት ወለል እየረገጡ መግባትና መውጣት ፣መረጃ አምጡ እየተባሉ በሌሊት መቀስቀስ፤የንጽህና ቁሳቁስ በጊዜ አለማግኘት፤ሽንት ቤት በወረፋ መጠቀም፤የገላ መታጠቢያ ውሃ ማጣት በሆስፒታሉ ታካሚዎች የተነሱ ቅሬታዎች ናቸው፡፡

የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ የተጠቀሱት ችግሮች ከሞላ ጎደል እየተስተካከሉ ቢመጡም ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ የሉም ለማለት ግን እንደማይቻል ተናግረዋል ምንም እንኳን በኤካ ኮተቤ ታማሚዎች ምንም ዓይነት ሕክምና እንደማይደረግላቸው፣ ክትትሉም ስማቸውንና ምን እንደሚሰማቸው ከመጠየቅ የዘለለ እንዳልሆነ ቢናገሩም፣ በየጊዜው እያገገሙ የሚወጡ ታማሚዎች ሕክምና አግኝተው እየዳኑ እንዳሉ ዶክተር ተገኔ ተናግረዋል ሲል ሪፖርተር ዘግቧል፡፡