አባይ ሚዲያ ሰኔ 03፤2012

አለም አቀፍ ወርሽኝ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማከናወን እንደማይችል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማሳወቁ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም ይረዳ ዘንድ ከቀረቡ አራት የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ የህገ መንግስት ትርጓሜ ላይ አጣሪ ጉባኤ ተቋቁሞ ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል ይህንንም መሰረት በማድረግ ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ውይይት የውሳኔ ሃሳቡን ተቀብሎ በ114 ድጋፍ፣ በአራት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል።

ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሺኙ ስጋት ሆኖ እስካለበት ድረስ የሁሉም ምክር ቤቶች ስልጣን እንዲቀጥል፤ እንዲሁም ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑ አለም ዓቀፍ የጤና ተቋም ሲያረጋግጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ ካጸደቀ በኋላ ከ9 ወር እስከ አንድ ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይካሄድ የሚለው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ነው ውሳኔ ያሳለፈው።

በሌላ መረጃ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ /ኦፌኮ / ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ምርጫን በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽ ከምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ሚደቅሳ ጋር ጠንከር ያለ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ በምርጫ ቦርድ ላይ ያለንን እምነት አጥተናል ብለዋል፡፡

ለዚህም   ሰብሳቢዋ ምርጫ ማካሄድ አንችልም ማለታቸውና ከዚያ በስተጀርባ ያሉትን ነገሮች እነደ ፖለቲከኛ ለመጠርጠር ተገደናል ሲሉ ተናግረዋል ፕሮፌሰር መራራ ለገባንበት ችግር አንድን አንቀጽ መንግስትን በሚጠቅምና ስልጣንን ለማራዘም በሚረዳ መልኩ ለመተርጎም መጣሩ ተገቢ አይደለም ያሉ ሲሆን መፍቴሄውም ፖለቲካዊ እንደሆነ ገልጸዋል ፕሮፈሰሩ አያይዘውም ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሚሉት አገሪቷን የሚያሻግራት ብልጽግና ብቻ ሳይሆን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት  ድርድርና ምክክር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትሩ አመነስቲ ያወጣውን ሪፖርት ድርሰት ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን ፕሮፌሰር መራራ አንስተው ፤እንደዚህ አይነት መሬት የረገጡ እውነታዎች ሲወጡ መፈተሽ እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን እኛ ግን ሪፖርቱን ደግፈናል ብለዋል የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሁላችንም ተረባርበን ልንደግፈው የሚገባ ነው ፤ነገር ግን በግድቡ ዙሪያ ከግብጽ ጋር የሚሰሩ ባንዳዎች አሉ እያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከማሸማቀቅ ይልቅ አሳማኝ ማስረጃ ካለ ለህዝብ አቅርቦ ማጋለጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡