አባይ ሚዲያ ሰኔ 03፤2012

ለወራት ተቋርጦ የነበረው በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የህዳሴው ግድብን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር በደቡብ አፍሪካ፣ በአውሮፓ ሕብረትና በአሜሪካ ታዛቢነት ተጀምሯል ይሁን እንጂ በድርድሩ በታዛቢነት የሚሳተፉት አገራት ሚናን በተመለከተ ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ሃሳብ ላይ በተደራዳሪ አገራቱ መካከል መግባባት ላይ እንዳልተደረሰ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለውና ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የተራዘመ ድርድርና ውይይት ሲደረግበት የቆየው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከተው ድርድር መጀመሩን አስታውቋል አክሎም ይህ በሦስቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን ተመልክቷል።

ድርድሩ ቀደም ሲል ተሳታፊ ከነበረችው አሜሪካ በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የአውሮፓ ሕብረት  በታዛቢነት በተገኙበት በትላንትናው እለት ማለትም ማክሰኞ ሰኔ 2ቀን 2012 ዓ.ም በበይነ-መረብ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት በአገራቱ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ነው የተካሄደው በዚህ ከወራት በኋላ በተካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ ተሳታፊ አገራቱ ስለድርድሩ የአካሄድ ሥነ ሥርዓት፣ ስለታዛቢዎችና ሌሎች ዋና ዋና ያልተቋጩ ጉዳዮችን በተመለከተ መወያየታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ተደራዳሪ አገራቱ ቁልፍ የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች በዝርዝር አቅርበው በቀጣይ ቀናት ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል ተብሏል ስምምነት ባልተደረሰበት የድርድሩ ታዛቢዎች ሚናን በሚመለከት ያለውን ልዩነት ላይ መፍትሄ ለማግኘትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስብሰባው በዛሬው ዕለት የሚቀጥል ይሆናል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ “የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ ናት” ብሏል።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ልማትን ለማፋጠን መሆኑን በተደጋጋሚ ብትገልጽም በግብጽ በኩል ከናይል የማገኘው የውኃ መጠን ይቀንሳል የሚል ቅሬታ የተነሳ ሲሆን ሱዳን በአንጻሩ የግድቡን መገንባት እንደማትቃወም ስትገልጽ ቆይታለች ባሳለፍነው ሰኞ ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተገኝተው ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ስድስት ዓመት በዘገየው የህዳሴ ግድብ 6 ቢሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ ማጣቷን በማስታወስ ከለውጡ በኋላ ፕሮጀክቱ እንዴት እንደዳነ፤ “የምክር ቤት አባላት ሄዳችሁ ማየት ትችላላችሁ” ብለው ነበር ጠቅላይ ሚንስትሩ አያይዘውም “ልመናና የሰው ደጅ መጥናት ሰልችቶናል ሰባ ፐርሰንት ወጣት ይዘን ስንዴ መለመን መቆም አለበት ያሉ ሲሆን የምንፈልገው ልመናን ማቆም ነው፣ ከዛ ውጪ ማንንም የመጉዳት ፍላጎትም፣ ታሪክም የለንም” ማለታቸው ይታወቃል፡፡