አባይ ሚዲያ ሰኔ 07፤2012

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የእንቦጭ አረም ከጣና ሐይቅ ውጪ በአባይ ወንዝ ላይ መከሰቱ በግንባታ ላይ ለሚገኘው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ ስጋት ይሆናል ሲል አስታውቋል የኢዜማ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ቡድን አርብ ሰኔ 05 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ምጥን ፖሊሲ፣ አረሙ የጣና ሐይቅ ላይም ሆነ የአባይ ወንዝ ላይ መከሰቱ ከፍተኛ ስጋት እንደደቀነበት አስረድቶ ተገቢው ግንዛቤ እንዲወሰድ እና ለግድቡ ግንባታ ከተሰጠው ትኩረት ያልተናነሰ አረሙን ለማስወገድ ትኩረት በመስጠት አረሙን የማስወገድ ሥራው መጠናከር እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ኢዜማ፣ አረሙ በአባይ ውሃ አማካይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር ሊደርስ እንደሚችል አያጠያይቅም ያለ ሲሆን አረሙን ተረባርቦ ማጥፋት አባይ እና ጣናን መታደግ ብቻ ሳይሆን የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራትን ልማት መታደግም ነው ሲል በጥናቱ አመልክቷል በጥናቱ የጣና ሐይቅ አሁን የተጋረጠበት አደጋ በምን የተነሳ እንደተከሰተበት ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን ፤ዋና ዋና ከተባሉት ምክንያቶች መኻልም የጣና ሐይቅ በዙሪያው ያሉ የእፅዋት ሽፋን መውደምና በገባር ወንዞቹ አማካኝነት ደለል ወደ ሐይቁ በብዛት መግባት፣ የእምቦጭ አረም መስፋፋት፣ መከላከያ ተከላ ሳይኖረው ውሃው ዳርቻ መታረስ፣ በዙሪያው የከተሞች መስፋፋት እና የአካባቢ ጥበቃ ያለማድረግ፣ የመኖሪያ እና የፋብሪካ ቆሻሻ ወደ ሐይቁ መለቀቅ በጣና ላይ ከፍተኛ የመጥፋት ስጋት ያሳደሩ ችግሮች ናቸው ተብሎ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ፓርቲው የእምቦጭ አረምን ለመከላከልና ጣናን ለመታደግ መወሰድ ያለባቸው ያላቸውን እርምጃዎች በጥናቱ ላይ ጠቁሟል ኢዜማ መፍትሔ ሲል ያቀረበው ምክረ ሀሳብ መኻል ዘላቂነት ያለው የተቀናጀ የተፋሰስ የልማት እቅድ በማውጣት የተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር፣ ዘላቂነት ያለው የእንቦጭ አረም ማስወገድ ስትራቴጂ መቀየስና መተግበር እና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ የድርድር አካል ማድረግ የሚል ይገኝበታል፡፡

በጥናቱ የማጠቃለያ ሀሳብ ላይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ አረም በአስቸኳይ ማፅዳት እንደሚገባና ለግድቡ ግንባታ ከተሰጠው ትኩረት ባላነሰ እንቦጭን ከጣና ለማስወገድ መሰጠት እንደሚኖርበት ኢዜማ አሳስቧል እንቦጭ አረም በኢትዮጵያ 2004 ዓ.ም መከሰቱን በጥናቱ ላይ የጠቀሰው ኢዜማ፣ አረሙን የማስወገድ ሥራ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ከመገንባት ጎን ለጎን መካሄድ ነበረበት ብሏል በመንግሥት በኩል እስካሁን እንደተካሄዱ ሲገለፅ የነበረው የደን ልማትና የተፋሰስ ጥበቃ ሥራዎችም ከሪፖርትነት በዘለለ መሬት ላይ የማይታዩ በመሆናቸው መንግሥት ክፍተቶቹን በመለየት የትግበራ መርሃ ግብር እና ተጠያቂ የሚሆን ባለቤት አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባት ይኖርበታል ሲል ኢዜማ ማሳሰቢያውን ሰጥቷል፡፡