አባይ ሚዲያ ሰኔ 08፤2012

በምዕራብ ኦሮሚያ ነቀምት ከተማ ትላንት እሁድ ሰኔ 7/ 2012 በነቀምት ከተማ አስተዳደር ጸጥታና ደህንነት ቢሮ ላይ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአባይ ሚዲያ ተናግረዋል ነዋሪዎች የትላንቱን ጥቃት በሚመለከት ሃላፊነት የወሰደ አካል ራሱን ባይገልጽም የተለመደው የሸኔ ታጣቂ ቡድን እንደሚሆን ነግረውናል፡፡

ከቀናት በፊት አባይ ሚዲያ ያነጋገራቸው የነቀምት ከተማ ነዋሪዎች  በአካባቢው ያለው የእንቅስቃሴዎች መገደብ፤ የንግድ ተቋማት፤ ሱቆችና ባንኮች መዘጋጋት እንዲሁም የመንገዶች ከመኪናዎች እንቅስቃሴ መታቀብ ውጥረቱ ወደ ምን ያመራ ይሆን የሚል ስጋት እንደደቀነባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዛሬው ዕለት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ደግሞ ባለፈው ሳምንት አካባቢ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ በመጠኑም ቢሆን ወደ ወትሮው ኑሮ እየተመለሰ መሆኑንና ባንኮችና የንግድ ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡና ተቋማት እንዲዘጉ ትዕዛዝ እያስተላለፈ ያለው ህገወጡ ታጣቂ ሀይል  እንደሆነ የገለጹልን ነዋሪዎች አሁንም ቢሆን በነዋሪዎች ዘንድ የነገሰው ስጋት መቀጠሉን ያስረዳሉ፡፡

ትላንት በነቀምት ከተማ አስተዳደር ጸጥታና ደህንነት ቢሮ ላይ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት እንደ አብነት ያነሱት ነዋሪዎች እንደሚሉት የተፈጸመውን የቦምብ ፍንዳታ ተከትሎ የአካባቢው የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ መረጃ እናጣራለን በሚል በንጹሃን ላይ እንግልት መፈጸማቸውን አብራርተዋል፡፡

የጸጥታ ሀይሎች በአካበቢው ወዳለ የፕሮቴስታንት እምነት ተቋም በማቅናት ከእዚሁ የቦምብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ የጠረጠሯቸውን ሰዎች ሲያዋክቡና መረጃ ለማወጣጣት ሲሞክሩ እንደነበርም የአይን እማኞች ለአባይ ሚዲያ አረጋግጠዋል ከሁለት ወር ገደማ በፊት የነቀምት ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አመራር ከኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተተከሶሰ ጥይት መገደላቸው አይዘነጋም በዚህ አካባቢው ዋናው ችግር አሁንም ድረስ ህዝቡን ነጻ አወጣለሁ ባለው ታጣቂ ሃይልና የህዝቡን ደህንነት አስከብራለሁ በሚለው የመንግስት የጸጥታ ሀይል መካከል የቀጠለው ግጭት ለንጹሃን መገደልና እስር ምክናየት መሆኑ ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአባይ ሚዲያ ይናገራሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ሆነ የሀገሪቱ መከላከያ ሀይል በተደጋጋሚ ባቀረቧቸው ማብራሪያዎች በህገወጡ ሸማቂ ቡድን ጋር በሚወሰዱ እርምጃዎች ንጹሃን እንደማይጎዱ ቢገልጹም አሁንም ግን ባልተረጋገጡ መረጃዎች በየከተሞቹ ላይ ችግር ሲፈጠር የመንግስት የጸጥታ ሀይል በአቅራቢያው ያገኘው ሰው ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ነዋሪዎች ያስረዳሉ በኦሮሚያ ክልል ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ሁከቶችና መንገድ የመዝጋት እንቅስቃሴዎች ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር የሚጻረሩ እንደሆነ የሚገልጸው የክልሉ መንግስት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን ለህብረተሰቡ ማስተላለፉን ቀጥሏል፡፡