አባይ ሚዲያ ሰኔ 10፤2012

የወላይታ ዞንን የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ ክብር ያለው ምላሽ በክልል ምክር ቤቱ ለወላይታ ተወካዮች አልተሰጠም ብለው የዞኑ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዋን ጨምሮ ሌሎች አባላት ከምክር ቤቱ ጋር መቆየት ትርጉም የሌለው ጉዳይ በመሆኑ ከምክር ቤት አባልነት ራሳችንን አግልለናል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ነገር ግን በደቡብ ክልል ምክር ቤት 38 መቀመጫ ያላቸው የወላይታ ዞን ተወከዮች ከምክር ቤት ተወካይነት ራሳቸውን ማግለላቸውን ቢናገሩም ፤የክልሉ ምክር ቤት ግን ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስታውቋል የደቡብ ክልል ምክር ቤት የስራ ሃላፊም ከወላታ ዞን ተወላጅ የምክር ቤት ተወካዮች  በደብዳቤ የደረሰን ነገር ስለሌለ ፤በጉዳዩ ዙሪያ ለመናገር ፍቃደኛ አይደለንም ብለዋል፡፡

የስራ ሃላፊው አክለውም በሁለት ቀናት ውስጥ ጉባኤ ለማድረግ የክልሉን ምክር ቤት አባላት መጥራታቸውን ተናግረዋል ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳባቸውን የሰጡት የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ /ዎብን /የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ማቲያስ ባልቻ በክልሉ ምክር ቤት የወላይታ ህዝብ ድምጽ እስካልተሰማ ድረስ የዞኑ ተወላጅ የምክር ቤት አባላት መሳተፍ የለባቸውም የሚለውን ሃሳብ በተለያየ መንገድ ስናነሳ ነበር ብለዋል፡፡

አቶ ማቲያስ የክልል ምክር ቤቱ አባላት ውሳኔ የዘገየ ቢሆንም ተገቢ ነው ብለን እናምናለን ሲሉ አስረድተዋል አባላቱ የብልጽግና ፓርቲ ውክልና ቢኖራቸውም የመረጣቸው ህዝቡ ነው ያሉት አቶ ማቲያስ ፤ህዝቡ ደግሞ ድምጻችንን የማያስተናግድና እኛ ፈርመን ላቀረብነው ጥያቄ ክብር የሌለው ምክር ቤት ውስጥ መቆየት የለባቸውም ብሏል ሲሉ አቶ ማቲያስ ተናግረዋል፡፡

አቶ ማቲያስ አክለውም የወላይታ ዞን  የራሱ ምክር ቤት ያለው ሲሆን አሁን ደግሞ በዞኑ ምክር ቤት ያሉ አባላት ውክልናቸውን ስላላነሱና  የቆመውም የክልል ምክር ቤት ተሳትፏቸው  ብቻ በመሆኑ ከክልሉ ጋር ያለው መንግስታዊ ግንኙነት አይቋረጥም ብለዋል በተጨማሪም መንግስት ለተነሱ ጉዳዮች የሚሰጠው የምላሽ ሁኔታ እየታየ ፤ህዝቡ የማይደመጥ ከሆነ የዞኑ አመራሮችም ሃላፊነት በሚሰማው መንገድ ወደ ህዝቡ ትግል እንዲቀላቀሉ እንጠይቃለን ሲሉ አሳስበዋል የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ዎብን አስቀድሞም የወላይታን የክልልነት ጥያቄ ወደፊት ሲያስኬድ የነበረ ድርጅት በመሆኑ ፤አሁንም በተለያዩ ደረጃዎች ያሉና የወላይታን የክልልነት ጥያቄ ወደፊት ከሚያስኬዱ ሰዎች ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡