አባይ ሚዲያ ሰኔ 11፤2012

‹‹የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በወቅቱ ቦርድ ሰብሳቢ በነበሩት ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል አድራጊ ፈጣሪነት በፍጥነት ተዳክሞ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል›› ሲሉ የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና፤ በሩሲያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ አስታወቁ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣ የህዳሴ ግድቡ አቶ መለስ በህይወት እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ በየወሩ ይገመገም የነበረ ሲሆን ከእርሳቸው ህልፈት በኋላ በየወሩ መገምገሙ ቀርቷል፡፡

የወቅቱ የቦርድ ሰብሳቢ በክላስተር አደረጃጀት በሁለት ወር አንድ ጊዜ እንዲታይ ብለው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አስታውሰው ፣ ሰብሳቢው አሠራሩን ተግባራዊ ሳያደርጉ መቅረታቸውንም አመልክተዋል በዚህ ሁኔታ የህዳሴ ግድቡን ፕሮጀክት የመብራት ኃይል ቦርድ አካልም ይገመግመው እንዳልነበር ጠቁመዋል የዘርፉ ባለቤት ብንሆንም ተገልለን ነበር፤ ሪፖርትም ከመብራት ኃይል እየወሰድን ጉድለቶቹን እንናገር ነበር ሲሉም ተናግረዋል::

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከመብራት ኃይል የሚያገኘውን መረጃ ይዞ እንደ ዘርፍ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት እንኳን ‹‹ምን አግብቷችሁ ነው መግለጫ የምትሰጡት›› በማለት በቦርድ ሰብሳቢው በኩል ቁጣ ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል በዚህ ሁኔታም ፕሮጀክቱ ከህዝብ ፕሮጀክትነቱ ወርዶ የአንድ ግለሰብ ፕሮጀክት ሆኖ እንደነበር አመልክተዋል።

በወቅቱ የህዳሴ ግድቡ ሥራና ውሳኔዎች በሰብሳቢው ውሳኔ ስር የነበሩ መሆናቸው ትክክል እንዳልሆነ ለቦርድ አባላት ቢነገርም የቦርድ አባላትም ፕሮጀክቱን እንደማይገመግሙ ማስታወቃቸውን አመልክተው፤ ግንባታው በአካል ባለመገምገሙ ብቻ ትልቅ ውድቀት እንደነበር ገልጸዋል ‹‹አቶ ኃይለማርያም በወቅቱ በጠሩትና በገመገሙት ስብሰባ ላይ ፕሮጀክቱ መዘግየቱ መግባባት ላይ ተደርሶ ሳሊኒም ሜቴክ ባልሠራቸው ሥራዎች ምክንያት የራሱን ሥራ መሥራት እንዳልቻለ ተነስቷል፡፡

በዚህ ወቅትም ቢሆን ለሥራው መጓተት ዋናው ምክንያት ሜቴክ እንደሆነ በመረጋገጡ ቦርዱ ዕርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ቢቀመጥም ማስተካከል ሳይቻል ቀርቷል›› ሲሉ ተናግረዋል የሚያሳዝነው ፕሮጀክቱ ምንም ለውጥ ሳይመጣ በሜቴክ በኩል ይሠራሉ የተባሉት ሥራዎች ሳይሠሩ ቦርድ ሰብሳቢው ለሜቴክ ሽፋን በመሆን ፕሮጀክቱ ‹‹ባለህበት ሂድ›› ሆኖ እንዲቀር ትልቅ በደል በሀገርና በህዝብ ላይ መሠራቱን አመልክተዋል፡፡

አሁን ያለው ለውጥ ባይመጣ ሜቴክን ይዞ የመቀጠል አቋማቸው የፀና እንደነበር አቶ አለማየሁ አመልክተዋል በጉዳዩ ዙሪያ የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድርና የቀድሞው የህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩትን ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልንና የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊበስልክ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን አዲስ ዘመን ጋዜጣ አስነብባለች።