አባይ ሚዲያ ሰኔ 11፤2012

የኢትዮጵያ፣የሱዳንና የግብጽ የቴክኒክና የህግ ቡድኖች ባደረጉት ወይይት “በጣም ወሳኝ በሆኑ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት”ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል መግለጫው ምንም እንኳን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት ቢደረስም ስምምነቱን ሙሉበሙሉ ለማጠናቀቅ በህግ ገዳዮች ላይ መስማማት ያስፈልጋል ብሏል፡፡

የሱዳን ልኡክ ቡድን የተደረሰበትን መሻሻል ሪፖርት በማድረግ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር መመሪያ ይቀበላል ያለው መግለጫው ስብስባው የተጠናቀቀው ሱዳን ምክክሯን ከጨረሰች በኋላ ለመቀጠል በመስማማት መሆኑን መገለጫው ገልጿል የግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ከአመታት በፊት ሱዳን ላይ በተፈረመው የመርሆች ስምምነት መሰረት መሆን አለበት ያለችው ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብጽ የሶስቱንም ሀገራት የጋራ ጥቅም ባስከበረ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጻለች፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስቴት ፕሮፌሰር ያሰር አባስ  በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ በግድቡ የቴክኒክ ጉዳይ 95 በመቶ መግባባት የተደረሰበት ሲሆን መግባባት ያልተደረሰባቸው የህግ ጉዳዮች በመሪዎች ደረጃ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ለሶስቱም ሀገራት መሪዎች ተልኳል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌትና አስተዳደር የሚመለከት የመርህ ስምምነት እንጂ አስገዳጅ ስምምነት አልፈርምም የሚል አቋም ማንጸባረቋ ከሱዳንና ግብጽ ጋር ልዩነት ውስጥ መግባቷን ፕ/ር ያሰር አባስ  ገልጸዋል ሚኒስትሩ አክለውም የሱዳን ፍላጎት ውይይቱ በግድቡ የውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ ያተኩር የሚል ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ  መግባባት ተችሏል ብለዋል፡፡

ይሁንና መግባባት ያልተደረሰባቸው የተለያዩ ህጋዊ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን ከነዚህም በኢትዮጵያ የተነሳው ከ10 ዓመት በኋላ የውሀ ክፍፍል እናድርግ የሚለው ሲጠቀስ በግብፅ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም የተደረሱ ስምምነቶች መፍረስ የለባቸውም እና ወደ ዋሽንግተን ድርድር ልንመለስ ይገባል የሚሉት ይገኛሉ ግብፅ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ያሉ ምስክሮች ባሉበት እንዲፈርሙ ትፈለልጋለችም ነው ያሉት ፕሮፌሰር ያሰር አባስ።

ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የመውሰድ አቋም እና ፍላጎት ቢኖራትም ሱዳንና አትዮጵያ ግን ልዩነቱ ወደ ጸጥታው ም/ቤት ሳያመራ በሦስትዮሽ ድርድር ሊፈታ ይችላል ብለው ያምናሉ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ልማትን ለማፋጠን መሆኑን በተደጋጋሚ ብትገልጽም በግብጽ በኩል ከናይል የማገኘው የውኃ መጠን ይቀንሳል የሚል ቅሬታ ሲነሳ  ፤ሱዳን በአንጻሩ የግድቡን መገንባት እንደማትቃወም ስትገልጽ ቆይታለች በመጭው ሀምሌ ወር የግድቡን ውሃ ሙሌት ለመጀመር ኢትዮጵያ እቅድ አውጥታ እየሰራች ሲሆን ሱዳንና ግብጽ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ሙሌቱ መጀመር የለበትም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡