አባይ ሚዲያ ሰኔ 11፤2012

ዴክሳሜታሶን ስለተባለውና ብዙ ስለተነገረለት መድኃኒት ዝርዝር ሁኔታና በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት መንገድ ምርመራ በማድረግ ሃሳብ እንዲያቀርቡ የተጠየቁት ባለሙያዎች፤ የደረሱበትን ውጤት ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማቅረባቸው ታውቋል በጤና ሚኒስቴር የህክምና ግልጋሎት ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ ያዕቆብ ሰማን ለቢቢሲ እንደገለጹት በመድኃኒቱ ላይ ምርመራውን እንዲያደርግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለተቋቋመው የባለሙያዎች አማካሪ ቡድን በሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ነው መመርያው ምርመራውን እንዲያደርጉ የተጠየቁት።

በዚህ መሰረትም ቡድኑ ይፋ የተደረገውን ሙሉውን ጥናት ከመረመረም በኋላ የደረሰበትን እንዲሁም ይሆናል ያለውን ምክረ ሐሳብ አቅርቧል ሲሉ አቶ ያቆብ  ገልፀዋል ባለሙያዎቹ በዴክሳሜታሶን ዙርያ የተደረገው ጥናትና ሙከራን በተመለከተ የተዘጋጀው ጭምቅ ሐሳብ ታትሞ ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ ስለመድኃኒቱ ጠቅላላ ይዘት እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል ስለሚችልበት ሁኔታ ጥናት በመድረግ ሐሳብ እንዳዘጋጁ ታውቋል።

አቶ ያዕቆብ እንዳሉት ዴክሳሜታሶን ከዚህም ቀደም ለተለያዩ በህመሞች ማከሚያነት ሲውል የነበረ መሆኑን አስታውሰው መድኃኒቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል በዚህም መሰረት በበርካታ መገናኛ ብዙሃን ተጋንኖ እንደተዘገበው ሳይሆን የመድኃኒቱ ፋይዳ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በፅኑ ሕክምና ላይ የሚገኙ ህሙማንን የሞት መጠን መቀነስ እንደሆነ፣ ይህ አዎንታዊ ጠቀሜታውም በቁጥር ደረጃ ሲሰላ አነስተኛ ነው ብለዋል።

“በማኅበረሰቡ ዘንድ መዘናጋትን እንዳይፈጠር እና አሁንም ዋነኛው መተኮር ያለበት መንገድ ባለሞያዎች የሚሰጧቸውን የመከላከያ እርምጃዎች መተግበር ነው ሲሉ” ገልጸዋል በርካሽ ዋጋና በስፋት የሚገኘው ዴክሳሜታሶን በኮቪድ-19 በጽኑ የታመሙ ሰዎች ሕይወትን ሊታደግ እንደሚችል የዩናይትድ ኪንግደም ባለሙያዎች ባደረጉት ምርምር እንደደረሱበት መግለጻቸው ይታወሳል።

በሙከራው ይህ መድኃኒት በኮሮናቫይረስ በጽኑ ከታመሙ ሦስት ሰዎች ውስጥ የአንዱን ሕይወት መታደግ እንደሚችል እና በወረርሽኙ ሰበብ ኦክስጂን በሚያስፈልጋቸው አምስት ሰዎች ላይ ሊያጋጥም የሚችልን አንድ ሞት ሊያስቀር እንደሚችል ተገልጿል ተመራማሪዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደተከሰተ በዩናይትድ ኪንግደም መድኃኒቱ በስፋት ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ እስካሁን ድረስ የ5000 ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ይቻል ነበር ብለዋል የዓለም የጤና ድርጅትም መድኃኒቱ በወረርሽኙ በተያዙ ጽኑ ህሙማን ላይ የሚኖረውን አውንታዊ ውጤት እንደተቀበለው ገልጿል ዴክሳሜታሶን እአአ ከ1960ዎቹ  ጀምሮ በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የሚያጋጥሙ እብጠቶችን ለመቀነስና የተወሰኑ አይነት የካንስር ህመሞችን ለማከም ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።