አባይ ሚዲያ ሰኔ 11፤2012

የሀይምኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በራሳቸው ተነሳሽነት በፌደራል መንግስቱና በትግራይ ክልል አመራሮች መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ተስፋ ሰጪ እንደነበር የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገልጸዋል ቀሲስ ታጋይ ታደለ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ማን “ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” ነው የሚባለው ያሉ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚሰራጨው ወሬ ፍጹም ከእውነት የራቀ ከመሆኑም በላይ ምናልባት ሀሳቦችን ወደሚፈልጉት መንገድ የሚቀይሩ አካላት የሚያሰራጩት ሊሆን ይችላል ብለዋልⵆ

በሌላ በኩል ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያው የመረጠው መንገድ ከማቀራረብ ይልቅ ማራራቅን ከማስታረቅ ይልቅ ማጣለትን ነው፤ በዚህም የፌደራል መንግስት እንዳይረጋጋ ክልሎችም ተደጋግፈው ሰላማቸውን በማስጠበቅ ልማታቸውን እንዳያስቀጥሉ በማድረግ አገር ማፍረስ ነው ፤ በመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ እየተዛመተ ያለው ነገር ሁሉ ከእውነታው ፍጹም ያፈነገጠ ነው ብለዋልⵆ

‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ እየሆነ ነው የእኛ ጉዞ ያሉት ቀሲስ ታጋይ አካሄዱም ጥሩ አይደለም  በመሆኑም ነገሮችን ከአዎንታዊ ገጽታቸው ይልቅ በአሉታዊ መንገድ እየወሰዱ የሚያራግቡ አካሎች ከስህተታቸው ሊታቀቡ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመቀሌው ውይይት ላይ የትግራይ አመራሮች ያነሱት ‘እናንተ አባቶች ውይይት ማድረግ አለባችሁ ማለታችሁን እንቀበላለን በእኛ በኩል ከጥር 2012 ዓም ጀምሮ ደብዳቤ ጽፈን ውይይት እንድናደርግ ጥያቄ አቅርበን መልሱን በመጠባበቅ ላይ ነን፤ ነገር ግን ለውይይት በራቸው ክፍት አይደለም’ ማለታቸውን አውስተዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም በፌደራል ደረጃ የውይይት መድረክ እንዲመቻች ጥያቄያቸውንም ማቅረባቸውንና ይህንን መሰረት በማድረግም እኛም ሀላፊነቱን ወስደን መድረኩን እንደምናመቻች ተማምነን ነው የተለያየነው ሲሉም ቀሲስ ታጋይ አስረድተዋል ከመቐሌ እንደተመለሱ ከብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ቀሲስ ታጋይ በዚህም በተነሱት እያንዳንዱ ነጥብ ላይ ምላሻቸውን እንዲሰጡ እንደተደረገና ፤ በፓርቲው በኩል የትግራይ ክልል የሀብት እንካፈል ጥያቄ እንጂ የውይይት ጥያቄ አለማቅረቡን እንደተገለጸላቸው ያብራራሉ፡፡

ሆኖም ለውይይት ጠይቀው የተዘጋ በር እንደሌለ አብራርትዋል በቀጣይም ቢሆን በሁሉም አለመግብባቶች ላይ ውይይት ለማድረግና ለመፍታት ፍላጎት እንዳላቸውና ዝግጁም እንደሆኑ መገለጹን ቀሲስ ታጋይ አብራርተዋል ከትላንት በስቲያ በመቀለ ከተካሄደው ውይይት በኋላ የትግራይ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ በሰጠው መግለጫ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት አገራዊ መድረክ ማዘጋጀት እንጂ ከህወሓት ጋር በድብቅ የሚደረግ ውይይትን አንቀበልም ማለቱ አይዘነጋም፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ዶ/ር ደብረጽዮንም “ውይይቱ በመጨረሻ ሰዓት የተጀመረ ቢሆንም መሞከሩ ግን ጥሩ ነው” ያሉ ሲሆን ጨምረውም “የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የሚንቀሳቀስ አካል ችግሩ የተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ በአገሪቱ አምባገነናዊ ሥርዓት ለመገንባት እየተሯሯጠ በሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ ነው ሲሉም ወቅሰዋል፡፡