አባይ ሚዲያ ሰኔ 13፤2012

በኢትዮጵያ ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን ሃገራዊ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌደረሽን ምክር ቤት  ምርጫው እንዲራዘም ቢወስንም ፤የትግራይ ክልላዊ መንግስት የምርጫውን መራዘም እንደማይደግፍና በክልል ደረጃ ግን ምርጫ እንደሚያካሂድ በማእከላዊ ኮሚቴው አማካኝነት መግለጹ አይዘነጋም፡፡

ይህንንም ተከትሎ የፌደራል መንግስትና የምርጫ ቦርድ ውሳኔው ተገቢ እንዳልሆነ ቢገልጹም ፤በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት አረና ትግራይ ለዲሞክራሲ እና አሲምባ ፓርቲዎች ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉላቸው በምርጫው እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል የአሲምባ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዶሪ አስገዶም ከአባይ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል አካሂደዋለው ስላለው ምርጫ የደረሰኝ ነገር የለም ስላለ ፤የክልሉ ምክር ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ ለምርጫ ቦርድ አቅርቦ ውሳኔ መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

አቶ ዶሪ አክለውም የምርጫው ውሳኔ ለምርጫ ቦርድ ቀርቦ ምርጫው እንዲካሄድ ውሳኔ ከተሰጠ በምርጫው እንደሚሳተፉ ገልጸዋል በሌላ በኩል ደግሞ የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብረሃ ደስታ  በክልሉ ይካሄዳል በተባለው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታዎችን አሰቀምጠናል ብለዋል አቶ አብረሃ ምርጫው በህጋዊና በገለልተኝነቱ ተቀባይነት ባገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዳኝነትና አስፈጻሚነት የሚከናወን ከሆነ ፣አረና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚሳተፍ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ፓርቲው ያለ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የሚካሄደው ክልላዊ ምርጫ በአጭር ጊዜ ውሰጥ ዝግጅቱ ተጠናቆ ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ? የሚቋቋመው ክልላዊ ምርጫ አስፈጻሚ ገለልተኛነቱ ምን ያህል ነው? እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ?የሚሉትን ሁሉ ይፈትሻል ሲሉ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል አረና በየኛውም መንገድ በአትዮጵያ አንድነት ላይ ስለማይደራደር፤ምርጫው የሚካሄደው ትግራይ አንድ የኢትዮጵያ ክልል ሆና ነው ወይስ ተገንጥላ?የሚሉ ጥያቄዎችን በሚገባ እንገመግማለን ብለዋል አቶ አብርሃ የተዘረዘሩት ጥያቄዎችና ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ የሚገኝ ምርጫ ከተካሄደ ፓርቲው ሊሳተፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡