አባይ ሚዲያ ሰኔ 13፤2012

ግብጽ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ጣልቃ እንዲገባ እንደምትፈልግ ገልጻለች ነገርግን ኢትዮጵያ የጸጥታውን ምክርቤት ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል አስታውቃለች ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ ባለፈው የካቲት ወር በዋሽንግተን ሲያካሂዱት የነበረውን ድርድር በኢትዮጵያ ተቃውሞ ምክንያት ሲጠበቅ የነበረው ስምምነት ሳይፈረም ተቋርጦ ነበር፡፡

ድርድሩ ሰኔ 2፣2012 ዓ.ም በድጋሚ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት እንዲጀመር ኢትዮጵያ ፈቃደኛ በመሆኗ ሊጀመር ችሏል በዚህ የድርድር ሂደት አሜሪካ፣የአውሮፓ ህብረትና ደቡብ አፍሪካ ታዛቢ የሆኑበት ድርድር የተካሄደ ሲሆን በወሳኝ የቴክኒክ ጉዳዮች ሲስማሙ በህግ ጉዳዮች ላይ ግን መስማማት እንዳልቻሉ ሀገራቱ አስታውቀዋል ኢትዮጵያ ግድቡን በመጭው ሀምሌ ወር መሙላት እንደምትጀምርና ይህ እቅድ ሊቀየር እንደማይችል እየገለጸች ነው፡፡

ከአባይ ሚዲያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር ዶ/ር ደረጄ ዘለቀ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ሰሞኑን ሲካሄድ የነበረውን የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት “ግብጽ ድርድሩን የምታቋርጥ ከሆነ ከዚህ በኀላ ለድርድር አንቀመጥም” ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአቶ ገዱ አቋም ኢትዮጵያን የሚጠቅምም አይደለም ያሉት ዶ/ር ደረጄ በሰላማዊ መንገድ ግጭትን የመፍታት ጥረት በሁለት ሶስቴ ሙከራ ካልተሳካ ይቀራል የሚባል ሳይሆን መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ሀገራት አለመግባባቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አለባቸው ብለዋል አንደራደርም ማለቱ ለግብፅ ሌላ ነጥብ ማስቆጠሪያ ዕድል ስለሚሰጣት ኢትዮጵያ በድርድር ውስጥ በመቆየት የግድቡ ውሃ መሙያ ጊዜ ሲደርስ ግድቡን መሙላትና ከዚያ ወደ ሚቀጥለው ድርድር መሸጋገር አለባት ብለዋል፡፡

ውድ የአባይ ሚዲያ ተመልካቾች በማለዳው የዜና እወጃችን ግብፅ ድርድሩን አቋርጣለች ብለን ዘግበን ነበር አሁን ማጣራት እንደተቻለው ግብፅ ድርድሩን አቋርጣ አልወጣችም ነገር ግን ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቅርቡ “ግብፅ አንድ እግሯን ድርድሩ ላይ፣ ሌላ እግሯን የፀጥታው ምክር ቤት ላይ አድርጋ ድርድሩን መቀጠል ትፈልጋለች” ማለታቸው አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ በሀገሪቱ ስላለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከሊቢያ ጋር አገሪቱ እያረገች ስላለው ጦርነት በተመለከተ ምንም ዓይነት ዘገባ እንዳይሰሩ የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኋን ካውንስል ማገዱን አስታውቋል ሀገሪቱ እርምጃውን የወሰደችው ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሚል ሽፋን ነው ተብሏል፡፡