አባይ ሚዲያ ሰኔ 13፤2012

በፌዴራል እና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለው ችግር በሠከነ ውይይት ሊፈታ ይገባል በሚል መነሻነት ባሳለፍነው ማክሰኞ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ ማምራታቸውንና በትላንትናው እለትም መግለጫ መስጠታቸውን ዘግበን ነበር ይህንንም ተከትሎ የሽማግሌው ቡድን አባል የሆነው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ ከአባይ ሚዲያ መስመር ላይ ዝግጅት ጋር ባደረገው ቆይታ በመቀሌና በአዲስ አበባ ስለነበረው የሽምግልና ሂደት ማብራሪያ ሰጥቶናል፡፡

አትሌት ሀይሌ በብልጽግናና በህወሀት መካከል ያለው ልዩነት የአይዶሎጂ ነው ብሎታል የሽምግልና ልኡኩ መቀሌ በተጓዘነትና አዲስ አበባ ተመልሶ ከብልጽግና አመራሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሁለቱም ወገን በኩል ቁጭ ብሎ ለመነጋገርና የተፈጠሩትን ችግሮችን ለመፍታት ተነሳሽነቱ መኖሩን አስተውያለሁ ያለ ሲሆን በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጠረው መካረር ወደ ጦርነት ያመራል ተብሎ መታሰብ እንደሌለበት ተናግሯል፡፡

ሁለቱም ወገኖች የገቡበትን እልህ ትተው ለህዝባቸው ሲሉ የግንኙነት መሻከሩ ሌላ መልክ ከመያዙ በፊት መነጋገር ግዴታቸው መሆኑንም ገልጿል ሽምግልና በባህሪው ከባድ መሆኑንና ጥፋተኛ ነህ መካስ አለብህ የተባለው ወገን እንዳይረካ የሚያደርግ ነው ስለሆነም ሁሉንም ወገን የሚያስደስት ውጤት ማግኘት ከባድ እንደሚያደርገው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ አስረድቷል፡፡