አባይ ሚዲያ ሰኔ 14፤2012

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጎበታል ተብሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ፣ ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይወያዩበት›› ተብሎ እንደተመለሰ በተነገረው የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ረቂቅ ላይ የመጨረሻ ውይይት እንዲያደርጉ የተጋበዙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በረቂቁ ላይ እንዲወያዩና አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከተጋበዙት ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ኦፌኮ፣ ኢሕአፓ፣ አብን፣ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲና ሌሎችም ፓርቲዎች ተገኝተዋል በረቂቁ ላይ የመጨረሻ ተወያይ ተደርገው የተጋበዙት፣ እውነተኛ ግብዓት አስተያየትና ሐሳብ እንዲሰጡ ሳይሆን ለይስሙላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሠሩት ለሕዝብና ለአገር ከመሆኑ አንፃር፣ በእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ላይ ምክክር ሲደረግ ዘመን ተሻጋሪ ሰነድ ሲዘጋጅ ሊወያዩበትና ካላቸው የፖለቲካ ፕሮግራም አኳያ አስተያየታቸውንና ሐሳባቸውን መግለጽ ሲገባቸው፣ ‹‹እንዳይጨቀጭቁን›› እና ‹‹አወያይተናቸዋል›› ብሎ በመገናኛ ብዙኃን ለመናገር የተደረገ ከአንገት በላይ የሆነ ጥሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቅሬታቸውም ዋና ምክንያት የፖሊሲ ረቂቁ ለምን ተዘጋጀ? ሳይሆን፣ እውነተኛ ውይይት ከተፈለገና የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ አስተያየትና ሐሳብን ለማካተት ተፈልጎ ከሆነ፣ ረቂቁ ከሁለትና ከሦስት ቀናት በፊት አስቀድሞ ሊሰጣቸው ሲገባ ውይይት በማድረጊያ ቀን መሰጠቱ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ቅሬታቸውን የገለጹት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ  ስለፖሊሲ ረቂቁ አጭር ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ነው ዶ/ር ጌታቸው የብሮድካስት ፈቃድን በሚመለከት እንዳስረዱት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያበረክቱት የካፒታልና የሙያ ሽግግር ለዘርፉ ዕድገት የራሱ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው፣ ውስን ድርሻ በመያዝ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እንዲሳተፉ በፖሊሲው መካተቱን አስረድተዋል፡፡

የውጭ አገር ዜጋም ሆነ፣ በውጭ አገር ዜጋ የተቋቋመ ድርጅት መከልከሉን አክለዋል የሃይማኖት ተቋማት አስተምህሮቶቻቸውን በሚመለከት ለሕዝቡ ለማስተላለፍ ከፈለጉ እሱን ብቻ ለማስተላለፍ እንደሚፈቀድላቸው በፖሊሲው የተካተተ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/99 የፖለቲካ ድርጅቶች ጭምር የብሮድካስት ፈቃድ እንደተከለከሉ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም የፖለቲካ ድርጅቶች ከሬዲዮና ቴሌቪዥን በስተቀር በሌሎቹ የኅትመትና የማኅበራዊ ድረ ገጾች መጠቀም እንደሚችሉም አስረድተዋል በፖሊሲ ረቂቁ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ውስጥ የጋዜጠኞች ‹‹ብሔርና›› የፆታ ስብጥር መረጋገጥ እንዳለበት የተካተተው ሐሳብ፣ ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል ተገቢ እንዳልሆነና አገር አቀፍ ይዘት ያለው የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ እንዲሆን ተደርጎ እንዲስተካከል ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት አንድ በሚመለከተው አስፈጻሚው አካል የተዘጋጀ ረቂቅ ፖሊሲ፣ አዋጅ ወይም ሌላ አገራዊ ሰነድ ላይ ለ‹ውይይት›› ተብለው የሚጋበዙት ሰነዱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊፀድቅ ጫፍ ከደረሰ በኋላ፣ ለይስሙላ መሆኑን ተወካዮቹ ተናግረዋል፡፡