አባይ ሚዲያ ሰኔ 14፤2012

በደቡብ ክልል የሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የዞን አስተባባሪዎች የፊታችን ሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች ጋር እንደሚወያዩ ፓርቲው አስታውቋል ውይይቱ ለግማሽ ቀን የሚዘልቅ ሲሆን የክልሉ አጠቃላይ ሁኔታ፣ ገዢው ፓርቲ ሊተገብረው ባሰበው አዲስ አከላለል እና በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የኢዜማ መዋቅሮች ወደፊት ሊከተሉ የሚገባው አቅጣጫ በውይይቱ ላይ ይነሳሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል መሆናቸውን ከሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ክፍል ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኢዜማ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዞኖች ካነሱት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ በመንግሥት በኩል ክልሉን አምስት ቦታዎች ለመከፋፈል የቀረበ ሀሳብ መኖሩን ገልፆ፤ በመንግሥት በኩል የቀረበው ምክረ ሀሳብ ሕገ ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሣሣይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ የሚሞክር እና ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው በማለት በመንግሥት በኩል የቀረበውን ምክረ ሀሳብ መተቸቱ የሚታወቅ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢዜማ በምዕራብ አባያ የብርብር ምርጫ ወረዳ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢያሱ አቦታ ለአስራ አምስት ቀን አላግባብ ታስረው ቢፈቱም በተያዙበት ቀን ከእጃቸው ላይ የተወሰደው የኢዜማ የምርጫ ወረዳው ማኅተም፣ የቃለ ጉባኤ መዝገብ፣ የአባላት ፎቶግራፍ፣ የአባላት መዝገብ እና የፕሮቶኮል መዝገብ እስካሁን ድረስ እንዳልተመለሰላቸው የኢዜማ የዞን አስተባባሪ ሉሉ መሰለ ገልጸዋል፡፡

የኢዜማ የምርጫ ወረዳ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በቁጥጥር ስር የዋሉት የወላይታን የክልልነት ጥያቄን በመደገፍ ፊርማ አስፈርመዋል በሚል ቢሆንም ፋይሎችን ከወሰዱና ከበረበሩ በኃላ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ብቻቸውን መንገድ ላይ የነበሩ ቢሆንም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ስብሰባ አድርጋችኋል በሚል ክሱን እንደቀየሩት የዞን አስተባባሪው ገልፀዋል።

የብርብር ምርጫ ወረዳ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ከአስራ አምስት ቀን እስር በኋላ በ2000 ብር ዋስ የተፈቱ ቢሆንም የተወሰዱት ንብረቶች ግን ሊመለሱላቸው እንዳልቻሉ የዞን አስተባባሪው ያሳወቁ ሲሆን በተለይ ማኅተሙን ለሌላ ነገር በማዋል ወንጀል ሊሠሩበት እንደሚችሉ ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል ከዚህ በተጨማሪም አቶ ኢያሱ ከታሰሩ ጀምሮ በገጠር ያሉ በወረዳዎች ላይ ያሉ አመራሮችና አባላት ማስፈራሪያ፣ በስልክ ዛቻ፣ እየደረሰባቸው አንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ስለጉዳዩ የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዋሲሁን ተስፋዬ ተጠይቀው ከእስር መልስ ንብረት እንዲመለስላቸው በተደጋጋሚ ሄደው ቢጠይቁም ቀና መልስ እንዳልተገኘ ገልፀዋል «ማኅተሙን ጨምሮ የወሰዱትን ንብረቶች ሊመልሱ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ የወረዳ ካድሬዎች እየሠሩ ያሉትን ለሕዝብ እናጋልጣለን፡፡» ሲሉም ሃላፊው መግለጻቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡