አባይ ሚዲያ ሰኔ 14፤2012

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት የተደረገውን ሕዝበ ውሳኔ ተከትሎ፣ ሲጠበቅ የነበረው ከነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጋር የሚደረገው የሥልጣን ርክክብ ሐሙስ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ተከናውኗል ነገር ግን የሲዳማና የደቡብ ክልል የሥልጣን ርክክብ መደረጉ ከሕዝበ ውሳኔው ቀጥሎ የሲዳማ ብሔር በክልልነት እንዲቋቋም የመጀመርያው ሒደት ቢሆንም፣ ካሁን በኋላ የሚጠበቁና መከናወን ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ ዕሙን ነው፡፡

በሲዳማ ክልልና በነባሩ የደቡብ ክልል መካከል የሚኖሩ የንብረት ክፍፍልና በአዲሱ ክልል የሚኖሩ አናሳ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች መብት ጉዳይ እንዴት እንደሚሆን በሕግ መደንገግ እንደሚኖርበት ካሁን ቀደም ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ይኼንን ለመግዛት የሚያግዙ የአናሳ ቁጥር ብሔሮች መብትና የንብረት ክፍፍልን የሚመለከት ሕግ ተዘጋጅቷል‹‹ክልሉም ሆነ ልምምዱ በኢትዮጵያ አዲስ እንደ መሆኑ መጠን አዳዲስ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፤›› የሚሉት የህገ መንግስት መምህር  የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ካሳሁን፣ ሐዋሳም መንታ አገልግሎት ስለሚሰጥ የዚህ አካል ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሚነሳው ጥያቄ ቀጣዩ አዲስ ክልላዊ መንግሥት እንዴት ሊመሠረት ይችላል የሚለው እንደሆነ የሚጠቁሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ሕገ መንግሥት ማርቀቅና ማፅደቅ፣ እንዲሁም ሦስቱን የመንግሥት አካላት ማዋቀር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ እነዚህን የመንግሥት ሦስቱ አካላት ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ለማቋቋም ደግሞ በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤት ያስፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይኼንን ለማድረግ ደግሞ ምርጫ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ማድረግ ስለማይቻል አሁን የሽግግር መንግሥት ማቋቋም መፍትሔ ሊሆን ይችላል ስለዚህ ይኼ የሽግግር መንግሥት ሕገ መንግሥት ለማፅደቅና መንግሥታዊ መዋቅር ለመሥራት አይችልም፤›› በማለት ያክላሉ ውክልናን በተመለከተ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ተወካዮች ተመራጭ በመሆናቸው፣ ከክልሉ ምክር ቤት እንደሚለቁና በፌዴራል ፓርላማ ደቡብን በመወከል የተመረጡ የሲዳማ ብሔር ተወካዮች ሲዳማን በመወከል መቀጠል እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ ክልል ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል ራሱን የቻለ ሥራ እንደሚጠይቅ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፣ የጋራ ሥልጣንና ሀብት አሰባሰብና አጠቃቀምን በተመለከተም መሠራት አለበት ይላሉ ያም ሆነ ይህ የሲዳማ ክልል ከተቋቋመ በኋላ የሚቀረው የደቡብ ክልል እንዴት ይቀጥላል የሚለው ጥያቄ በርካቶችን የሚነጋገሩበት ጉዳይ ሲሆን፣ በተለይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የተቀረውን የደቡብ ክልል አደረጃጀት በአጀንዳነት ቢይዝም ሰፊ ውይይት ያልተደረገበት ጉዳይ መሆኑ ጥያቄዎች እያስነሳ ይገኛል፡፡

ይህን ጉዳይ ምክር ቤቱ በአጀንዳነት ቢይዘውም በፌዴራል መንግሥት ደረጃ  ጥናት እየተደረገበት እንደሆነ ከመግለጽ ባለፈ፣ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት እንዳልተደረገበትም ለማወቅ ተችሏል የደቡብ ክልል እንዳዲስ እንዲዋቀር የወጡት ምክረ ሐሳቦች የሲዳማ ክልልን መውጣት ከግንዛቤ ሳይከቱ የደቡብ ክልልን በአራት የሚከፍሉ ሲሆኑ እነሱም ደቡብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ኦሞቲክና የሲዳማ ክላስተር በሚል ተከፋፍለዋል፡፡