አባይ ሚዲያ ሰኔ 14፤2012

ግብጽ የህዳሴ ግድቡ ላይ በሚደረጉ ድርድሮች ወቅት ‘የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ተፈፃሚ አይሆኑም’ በሚል በኢትዮጵያ ዘንድ የሚነሳው ጥያቄ አግባብ አይደለም፤ ስምምነቶቹ አሁንም ተፈፃሚ ናቸው ስትል ከትናንት በስቲያ በድጋሚ ለጸጥታው ምክር ቤት በላከችው አቤቱታ አመልክታለች።

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በማመልከቻቸው አባሪ ላይ ኢትዮጵያ በ1894 ዓ.ም ከታላቋ ብሪታኒያ እና ከጣሊያን ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ዋቢ በማድረግ “ውሉ ተፈጻሚ ነው” ሲሉ መከራከሪያ አቅርበዋል ሳሜህ “ኢትዮጵያ በቅኝ ተገዝታ አታውቅም። አባይን በተመለከተ የፈረመቻቸው ማንኛውም አይነት ስምምነቶች ነፃ አገር ሆና ስለፈረመቻቸው ገዢ ናቸው” ሲሉም ሞግተዋል።

ግብጽ በአጼ ምኒልክ በኩል የተፈረመውን ስምምነትም አባሪ አድርጋ ለምክር ቤቱ የላከች ሲሆን የስምምነቱ አንቀጽ ሶስት “ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ፣ በጣና ብሎም በሶባት ላይ ምንም አይነት ግንባታ አታከናውንም፤ እንዲከናወንም ፈቃድ አትሰጥም” ይላል ነገር ግን ከታላቋ ብሪታኒያ ንግስት እና ከሱዳን ጋር ስምምነት በማድረግ ግንባታዎች ሊካሄዱ እንደሚችሉ የ1984ቱ ስምምነት ያትታል ይህንን ተከትሎ ግብጽ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያለ ስምምነት የሚሞላ ከሆነ ዓለማቀፍ ሰላም እና ደህንንነትን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ አጸፋዊ እርምጃዎች ልትወሰድ እንደምትችልም አስጠንቅቃለች።

ግብጽ ለዚህ ዛቻዋ መሰረት ያደረገችው የተባበበሩት መንግስታትን ቻርተር ነው። “የህዳሴ ግድቡ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። 100 ሚሊዮን ግብጻዊያንም ህይወታቸው በዚሁ ወንዝ ላይ የሚመሰረት በመሆኑ ያለ ስምምነት ግድቡን መሙላትም ሆነ ወደ ስራ ማስገባት ወሳኝ ብሔራዊ ጥቅማችን ይነካል” ሲሉ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በማመልከቻቸው ላይ ገልጸዋል። “ማንኛውም የተባበሩት መንግስታት አባል አገር ወሳኝ ብሄራዊ ጥቅሙን የመጠበቅ መብት አለው” ያለችው ግብጽ ስለዚህም “አጸፋውን የመመለስ መብት” እንዳላት ለምክር ቤቱ አስረድታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽ ከአስዋን ግድብ በትነት የምታባክነው ውኃ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውኃ መሙላት የሚያስችል መሆኑን የምሥራቅ ናይል ቴክኒካዊ አኅጉራዊ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ገልጸዋል አቶ ፈቅ አሕመድ በድርድሩ ላይ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት፣ በራሷ ጉልበት እና በራሷ ገንዘብ በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሆኖም ለዓባይ ወንዝ ምንም አስተዋጽኦ የሌላት ነገር ግን የወንዙ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ግብጽ በግድቡ ላይ መርህ የሌለው ተቃውሞ እያሰማች መሆኑን አስረድተዋል የወንዙ እልፍ ዓመታት ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ግብጽ  በየዓመቱ ከአስዋን ግድብ በትነት የሚባክነውን ያክል ውኃ እንኳን ኢትዮጵያ ልትይዝ አይገባም የሚል ግትር አቋም መያዟን ገልጸዋል።