አባይ ሚዲያ ሰኔ 16፤2012

በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ዳጋም ወረዳ የአንድ አርሶ አደር መኖሪያ ቤት ከነሙሉ ንብረቱ ተቃጠለ ቤት የተቃጠለባቸው የአርሶ አደሩ ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ ድርጊት የተፈፀመው ከትላንት በስቲያ ማለትም እሁድ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ/ም ነው ቤቱ የተቃጠለባቸው አቶ ስዩም አዲኖ የተባሉ የ70 አመት አዛውንት አርሶ አደር ሲሆኑ የሳቸው ልጅ የሆነው ገዳ ስዩም የአባቱን ቤት ያቃጠለው የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ፖሊስ መሆኑን ይናገራል፡፡

ይህንንም ያደረጉት ልጃቹ ጫካ ነው ያለው አምጡት በሚል ነው ያለ ሲሆን እኛ እንደማንኛውም ልጅ እናስተምረዋለን ብለን ወደ ዩኒቨርሲቲ ላክነው ከዛ የት እንደሄደ አናውቅም ይላል ይሄ ጫካ ሸፍቶ ነው ያለው የሚባለው የአቶ ስዩም ልጅ በ2005 ዓ/ም የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ አመት የህግ ተማሪ እንደነበርና ከዛ በኋላም ወደ ቤተሰብ እንዳልተመለሰ ወንድሙ ገዳ ይናገራል፡፡

በዚህም የተነሳ ካለፈው አመት ጀምሮ የመንግስት ሃላፊዎች ቤተሰቡን ማስፈራራት እንደጀመሩና ልጁን አምጡት ያለበለዚያ ግን እንገድላቹሃለን ማለታቸውን ያስረዳል እኛም ልጁ ያለበትን ባለማወቃችን ሞትን መርጠን ቁጭ አልን ይላል ልጁ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ተማሪ የሚያስፈልገውን  አሟልተን ላክነው ከዛ ግን ስልኩም ዝግ ሆነ ልናገኘውም አልቻልንም በዚህም ምክንያት እያዘንን ነበር ይላል የአቶ ስዩም ልጅ፡፡

አሁን የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ እንደሚሰራ የሚናገረው ገዳ እኔ ለመንግስት ታማኝ ሆኜ የተሰጠኝን ሃላፊነት በአግባቡ እየተወጣሁ እያለ ቤተሰቤ ላይ የደረሰው አሳዝኖኛል ብሏል አባቴ እንኳን ስለፖለቲካ አሁን ያለውን መንግስት ስም እንኳን አያውቅም ሲልም ቤተሰቦቹ ምንም ጥፋት እንደሌለባቸው አስረድቷል ገዳ ስለተፈፀመው ድርጊትም ሲያስታውስ እሁድ ጠዋት 12 ሰአት ላይ ቁጥራቸው 30 የሚሆን ልዩ የፖሊስ ሀይሎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንደመጡና ቤተሰቡን ከቤት እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ ቤቱን ከነ ሙሉንብረቱ በእሳት እንዳያያዙት ተናግሯል፡፡

ልዩ ሀይሎቹ ቤቱን ካያያዙት በኋላም ሰዎች እሳቱን እንዳያጠፉ ሲከላከሉና ተቃጥሎ እስኪያልቅም ሲጠብቁ እንደነበር ገዳ የነበረውን ሁኔታ አስታውሷል በሁኔታው የተደናገጡት አባቱ ሸሽተው ወዴት እንደሄዱ እንደማያውቅ የተናገረው ገዳ ታናናሾቹን ጨምሮ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውን ገልጿል ስለጉዳዩ የተጠየቁት የዳጋም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌቱ ተፈሪ ስለተፈጠረው ነገር የማውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ታሪኩ ድሪባ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ፖሊስ የነዋሪዎችን ቤት የሚያቃጥልበት ምክንያት የለውም እኛም እንዲህ አይነት ትዕዛዝ አናስተላልፍም ብለው ለድርጊቱም በምዕራብ ወለጋ የሚንቀሳቀሰውን ኦነግ ሸኔን ተጠያቂ አድርገዋል ዘገባው የቢቢሲ ኦሮምኛ ክፍል ነው ከዚህ ቀደም የቀድሞውን የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ታጣቂዎች በጉጂ የጠንቋይ ቤት እያሉ የአንድን አርሶ አደር ቤት ሲያቃጥሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም በጉዳዩ ላይ አባይ ሚዲያ ያነጋገራቸው የብልፅግና አመራሩ አቶ ታዬ ደንደአ መንግስት ጉዳዩን እንደሚያጣራ መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡