አባይ ሚዲያ ሰኔ 17፤2012

ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች በጥይት ተደብድበው ሕይወታቸው ያለፈው ከፍተኛ የአማራ ክልል ባልሥልጣናትና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ላይ የተፈጸመው የወንጀል ድርጊት፣ በገለልተኛ ኮሚሽን ተጣርቶ ለሕዝብ እንዲገለጽ የሟቾች ቤተሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጽፈዋል ደብዳቤውም የሟቾች ቤተሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በቀጥታ ተጽፎ ለ15 ከፍተኛ የፌዴራል፣ የክልልና የሃይማኖት ተቋማት ግልባጭ የተደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሟቾች ቤተሰቦች በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው ‹‹ፍትሕ እንፈልጋለን›› ደብዳቤ እንደሚያብራራው፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል ባለሥልጣናትና በአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ላይ የተፈጸመው የወንጀል ድርጊት እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር አንገት የሚያስደፋ ነው በወንጀሉ አፈጻጸም ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የነበሩ ተዋንያን፣ በሐሳብ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ የደገፉ አካላት እንዳሉ የፀና እምነት እንዳላቸው ሠፍሯል፡፡

በክስ ሒደቱም ቁንጮ ተጠርጣሪዎችን ዘንግቶ ጥቂት የሒደቱ ተጠርጣሪዎችን ብቻ ማካተቱ፣ ይባስ ብሎም የአብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ክስ በፖለቲካ ውሳኔ መዘጋቱና ከእስር እንዲፈቱ መደረጉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የፍትሕ ጠበቃዎችን እንዳሳዘነ ገልጸዋል የአገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለጣሉበት ክህደታቸው ምንም ዓይነት የወንጀል ተጠያቂ ሳይሆኑ መቅረታቸው፣ አገራዊና ፖለቲካዊ የሽግግር ለውጡን ፍትሐዊነት አደጋ ላይ ጥሎታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

የክልል ፕሬዚዳንትና ሁለት ወሳኝ ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነውን የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ከእነጓደኛቸው ሕይወት እንዲቀጠፍ ያደረጉ ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል በወንጀሉ የተሳተፉ፣ በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች ለግድያው ተባባሪ የነበሩ ተጠያቂ ካለመደረጋቸውም በላይ፣ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩትም ተጠያቂ ሳይደረጉ ክሳቸው በፖለቲካ ውሳኔ መቋረጡ የወንጀሉ ተዋንያንን የልብ ልብ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸውም አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወንጀሉን ድርጊት አጣርቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውነታውን የሚገልጽ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዲቋቋም ትዕዛዝ እንዲሰጡላቸውና ወንጀሉን ያቀናበሩ፣ የተሳተፉ፣ ወንጀሉ እንዲፈጸም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ በነበሩ መንግሥታዊ አካላትና ተባባሪዎች ላይ ተገቢው ፍትሕ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው መኰንን ፣ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴና የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኰንንና የሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ሙት ዓመት በተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ሰኔ 13 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ተዘክሯል፡፡