አባይ ሚዲያ ሰኔ 17፤2012

በሁመራ በረከት አላው አካባቢ ከባድ መሳሪያዎች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የአካባቢው ምንጮች ገለጹ በትላንትናው ዕለት ማለትም ሰኔ 16/2012 ዓ/ም የሱዳን ጦር በሁመራ በኩል ተኩስ ከፍቶ እንደነበር ከአካባቢው ምንጮች ለአባይ ሚዲያ መረጃ ደርሶት ዘግበን ነበር በዛሬው ዕለትም አባይ ሚዲያ ከአካባቢው ምንጮቹ ማረጋገጥ እንደቻለው የተኩስ ልውውጡ ቢበርድም በሁመራ በረከት አላው ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የከባድ መሳሪያ እንቅስቃሴ ይስተዋላል፡፡

የግጭቱ መነሻ ምክንያት በሁለቱም በኩል እንዳይታረስ ተብሎ ለጊዜው ስምምነት ተደርጎበት የነበረን መሬት አንድ ባለሀብት በማረሱ እንደሆነ አንድ የአካባቢው ምንጫችን ነግረውናል ይህንንም ተከትሎ የሱዳን ሰራዊት ወደ እርሻ አካባቢው እንደመጣና በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ ድንበራችን አትግቡ ይህንን ነገር በውይይት ነው የምንፈታው ቢልም ከሱዳን ሰራዊት አንዱ ተኩሶ አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል መግደሉን ገልጸዋል፡፡

የአባሉን መገደል ተከትሎም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተከታትሎ ሀሸባ በሚባለው ቦታ አፀፋውን መመለሱን አስረድተዋል ከዚህ ክስተት በኋላም የአካባቢውን መሬት የያዙትን ባለሀብቶች ጨምሮ የአካባቢው ገበሬዎችም በግጭቱ ምክንያት የእርሻ መሳሪያቸውን ይዘው ለመውጣት መገደዳቸውን ምንጫችን ገልጸውልናል፡፡

ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ አለመግባባት መቀስቀሱን የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ማስታወቁን መዘገባችን አይዘነጋም የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ዶ/ር አሚን መሐመድ ሐሰን “የኢትዮጵያ ታጣቂዎች” አትባራ ወንዝ ውሃ ሊቀዱ በሄዱበት ወቅት ከሱዳን ወታደሮች ጋር አለመግባባት መፈጠሩንና አንድ ኮማንደር መሞቱንና ሌሎች ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸው ነበር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተገኝተው ምላሽ በሰጡበት ወቅት ጉዳዩ በማንሳት በውይይት የሚፈታ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡