አባይ ሚዲያ ሰኔ 18፤2012

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ግብዣ ወደ ካርቱም ማቅናታቸውን የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል ሶስት ቀናትን በሚዘልቀው የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑስማን ሳሌህ እና የፕሬዝዳንቱ የቅርብ አማካሪ የማነ ገብረ አብ ተካተዋል፡፡

አቶ የማነ ገብረ መስቀል እንዳስቀመጡት ከሆነ ጉብኘቱ በሃገራቱ የሁለትዮሽ እና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች እንዲሁም በቀጣናዊ የትብብር እና ውህደቶች ዙሪያ ያተኩራል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሱዳን ቆይታቸው በህዳሴ ግድቡ ሳቢያ በኢትዮጵያ፤ በሱዳንና በግብጽ መካከል የተፈጠረውን ተቃርኖ ለማረግብና ለማስማማት ሙከራ እንደሚያደርጉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት የሚያወጧቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ግብፅ በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር የውኃ ክፍፍልን እንዲያመለክት በመጠየቋ መግባባት አለመቻሉን ኢትዮጵያ ማሳወቋ ይታወሳል በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ዳግም ሲካሄድ የነበረው ድርድር በሱዳን ጥያቄ መሠረት ባለፈው ሳምንት ከተቋረጠ በኋላ፣ ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ በኢትዮጵያ ግትር አቋም ምክንያት ድርድሩ እንደተቋረጠ አቤቱታ አቅርባለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደግሞ ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሪቬሬ ሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ ግብፅ ላቀረበችው አቤቱታ ምላሽ ሰጥተዋል ግብፅ የውኃ ክፍፍልን አንስታ እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄም፣ የውኃ ክፍፍልን አስመልክቶ ወደፊት በሚደረግ ስምምነት ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ በተጨማሪ ያሏትን የውኃ ሀብቶች ከግምት አስገብቶ መፈጸም እንደሚገባውም አቶ  ገዱ ተናግረዋል።

አሜሪካ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲሰበሰብ ግብፅ ያቀረበችውን ሐሳብ ብትደግፍም፣ ተመድ ግን ሦስቱ አገሮች ልዩነቶቻቸውን ራሳቸው እንዲፈቱ ሲል ቻይና ደግሞ አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሔው ራሳቸው ዘንድ እንደሆነ ማስታወቋ ተሰምቷል የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የህዳሴ ግድቡን ውዝግብ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ሦስቱ አገሮች ልዩነቶቻቸውን በተፈራረሙት የትብብር መርህ መግለጫ ስምምነት መሠረት እንዲፈቱ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በህዳሴ ግድቡና በኢትዮጵያ የዓባይ ውኃን መጠቀም መብት ላይ ታጥቃ የተነሳችውን ግብፅ ድርጊት ያበሳጫቸው ኢትዮጵያዊያን፣ መንግሥት በሐምሌ ወር ግድቡን መሙላት እንዲጀምር ከማሳሰብ አልፈው ግፊት እያደረጉበት ነው ምናልባትም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሱዳን ለሶስት ቀናት በሚያደርጉት ቆይታ በህዳሴው ግድብ ድርድር ዙሪያ በሚያካሄዱት ምክክር በሚችሉት ሁሉ ጣልቃ በመግባት ውጥረቱን ያረግባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡