አባይ ሚዲያ ሰኔ 18፤2012

ዛሬ በዎላይታ በተለያዩ አከባቢዎች ሰሞኑን የምክርቤት አባላት ያስተላለፉት ውሳኔንና እርምጃ በመደገፍ የድጋፍ ሰልፎችና ስብሰባዎች ተካሄደዋል ሰሞኑን በደቡብ ክልል ምክርቤት ያሉ የዎላይታ ተመራጮች  ራሳቸውን ከምክርቤት አባልነት ያገለሉበትን ሂደትና የዎላይታ ዞን ምክርቤት የህዝቡ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ የወሰዷቸውን እርምጃዎችንና አቅጣጫዎችን በመደገፍና የህዝብ ጥያቄ ይመለስ የሚሉ ሰልፎችና ስብሰባዎች በዎላይታ በተለያዩ አካባቢዎች በዛሬው ዕለት መካሄዳቸው ታውቋል፡፡

ከሰልፎቹ ምስል እንደሚስተዋለው ቁጥሩ ትንሽ የማይባል የነዋሪዎች ስብስብ የወላይታን ክልል ይወክላል ያለው ባንዲራ በማንገብ አደባባይ ወጥቶ ውሏል በተለይም የኮሮና ቫይረስ ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት ህዝባዊ ሰልፎች መካሄዳቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር የሚጣረስ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የወላይታ ዞን ምክር ቤት  ሰኞ ሰኔ 15፤ 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም ውሳኔ በማሳለፍ የክልሉን መንግስት ለማደራጀት የሚያስችል ሴክሬቴሪያት ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋም እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም እንዲከናወኑ መወሰኑ ይታወቃል የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ “የወላይታ ህዝብ ጥያቄ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ነው” በማለት በዕለቱ የተላለፈው ውሳኔ ይህንን የተመለከተ እንደሆነ ገልጸዋል።

“የህዝቡ ጥያቄ ግልጽ እና ግልጽ ነው። ህዝቡ የጠየቀው መጠሪያው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት [ሆኖ] በዚህ ልክ የሚጠራው፣ የስራ ቋንቋው ወላይትኛ የሆነውን፣ ዋና መቀመጫው ወላይታ ሶዶ የሆነውን ክልል ለመመስረት ነው። ከዚህ ውጭ ያሉ አማራጮች ህዝቡ ያልጠየቀው ስለሆነ ተቀባይነት እንደማይኖረው ወስነናል” ብለዋል አቶ ዳጋቶ።

የወላይታ የክልልነት ጥያቄ በመንግስት በኩል “ባጠረ ጊዜ ይመለሳል የሚል እምነት አለን” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው “ጥያቄው ሲመለስ በቀጥታ እና በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት የሚያግዝ የሴክሬቴሪያት ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋም መወሰኑን በወቅቱ አውስተዋል ጽህፈት ቤቱ “የራሱ የሆነ በጀት ያለው እና በህዝብና በመንግስት የሚደገፍ ነው” ሲሆን “የተለያዩ ስራዎችን በባለቤትነት የሚሰራ ተቋም መቋቋም ስላለበት” ውሳኔው መተላለፉ ተነግሯል፡፡

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄውን ያቀረበው፤ ዞኑ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ ውሳኔ ባሳለፈ በዓመቱ፤ ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር ምክር ቤቱ ጥያቄውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ የወሰደው “የደቡብ ክልል ምክር ቤት “በክልል ለመደራጀት ላቀረብኩት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠኝም” በሚል ነው።

ባለፈው ጉባኤ የወላይታ የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ በወላይትኛ ቋንቋ ሲሰጡ የነበሩት አቶ ዳጋቶ በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ላይ “እምነት እንደሌላቸው” በግልጽ ተናግረዋል ዋና አስተዳዳሪው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ግን እምነት ያጡት በክልሉ የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት በዛሬው የወላይታ ሰልፍ ዙሪያ ከፖሊስ የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡