አባይ ሚዲያ ሰኔ 20፤2012

የህወሓት ነባር ታጋይ እና አሁን ላይ የአረና ትግራይ ስራ አስፈጻሚ አባል ታጋይ አረጋሽ አዳነ ያለፉትን ምርጫዎች ዛሬ ላይ መድገም በሰማዕታቱ ስምና ዓላማ መቀለድና ሰማዕታቱ የተሰዉት ለህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ቢሆንም የቀደሙት ምርጫዎች ይህንን ማረጋገጥ የቻሉ እንዳልነበሩም አስታወቀዋል።

ታጋይ አረጋሽ፤ የሰማዕታት ቃል እና ሰማዕታቱ የተሰዉለት ምርጫ ህዝብን ረስቶ ለራሱ ጥቅምና ፍላጎት ስልጣን መጨበጫ ሳይሆን ህዝብ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረት መሆኑን ተናግረዋል ታጋይ አረጋሽ እንደገለጹትም እስካሁን ትግራይ ላይ አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል፤ እነዚህ ምርጫዎች ግን ህገ መንግስቱ ላይ ያለውን የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጡ ምርጫዎች አልነበሩም፤ ሰማዕታት የተሰዉት ግን ህገ መንግስቱ የሚለው ነገር እንዲተገበር ነበር ይላሉ።

ስለዚህ ህውሓቶች የሰማዕታት አደራ ሊታሰባቸው የሚገባው አሁን ችግር ውስጥ ሲገቡ ሳይሆን፤ ቀድሞ በነበሩ ምርጫዎችም ጭምር ነበር ያሉት ታጋይ አረጋሽ ፤ እናም አሁን ችግር ውስጥ ከገቡ በኋላ የሰማዕታትን ተልዕኮ እናስፈጽማለን ብሎ መነሳት በሰማዕታት መቀለድ መሆኑን አብራርተዋል ታጋይ አረጋሽ ህወሓት አምስት ምርጫዎችን አሸንፎ እያስተዳደረ ባለው የትግራይ ክልል የሰማዕታቱ እምነት ተረስቶ፤ ከህዝብ ይልቅ የራስ ፍላጎት አይሎ ህዝቡ የስልጣን ባለቤትነቱን ተነፍጎ በፍትህ እጦት፣ በተበላሸ የመንግስት አስተዳደር፣ በሙስናና የዘመድ አሰራር እየተንገላታ እንደሚገኝም አመልክተዋል ።

ህወሓቶች አንዴ የሰማዕታትን ዓላማ መስመር ስተው ተሻግረው አልፈውታል ያሉ ሲሆን የተሳሳተ መስመር ደግሞ አጠቃላይ ሁኔታው ላይ ለውጥ በማድረግ እንጂ በዚህ አይነት ምርጫ አይደለም የሚካካሰውና የሚተካው ያሉት ታጋይ አረጋሽ ከዚህ ባለፈም ይሄን ያህል ምርጫ እናካሂዳለን ሲሉ ምርጫ ብቻውን ውጤት አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።

ታጋይ አረጋሽ ለዚህ ደግሞ በክልሉ ምቹ ሁኔታ እንደሌለና  እነሱን  የሚደግፉ ግን ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶችን  እያሳተፉ፤ ለየት ያለ ሀሳብ ያላቸውን ተፎካካሪዎች ግን መግፋት ብቻም ሳይሆን ስድብና ስም ማጥፋቶችን እየፈጸሙባቸው ነው። እናም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለት፤ በሰማዕታቱ ስምና ዓላማ መቀለድ ነው ብለዋል ።

የተሰዉ ታጋዮችም ከህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ ባለስልጣናት የግል ጥቅምና ፍላጎታቸውን ያስቀድማሉ የሚል ሀሳብ አልነበራቸውም፤ ያሉት ታጋይ አረጋሽ፣ ህወሓቶችም አሁን ጭንቅ ውስጥ ሲገቡ ሰማዕታትን እንደ መከለያና መሸፈኛ አድርገው የህዝቡን ስሜት በመቀስቀስ፤ ህዝቡን በቁስል ነካክቶም በእነርሱ ስር እንዲሰለፍ ለማድረግ እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸው፣ የትግራይ ህዝብም እውነታውን በአግባቡ እንዲያጤነው ጥሪ አቅርበዋል።