አባይ ሚዲያ ሰኔ 22፤2012

በቅርቡ ሶስቱን የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አዋህዶ ብልፅግናን ያቋቋመው ገዢው ፓርቲ ከህወሃት ጋር መካረር ውስጥ ከገባ ወራትን አስቆጥሯል የሁለቱ ፓርቲዎች መካረር በተለይም ምርጫ ይካሄዳል አይካሄድም የሚል ፍጥጫ ውስጥ ከገባ ደግሞ ሰነባብቷል የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ህወሃት ደግሞ በህዝቡ ላይ በደል እየፈጸመ እንደሆነ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡

በተለይም ደግሞ በትግራይ የብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ነብዩስሁል ሚካኤል በክልሉ ያለውን ችግር በፌስቡክ ገጻቸውና በሚሰጧቸው ቃለመጠይቆች ሲገልጹ ቆይተዋል በዛሬው ዕለትም በማህበራዊ ገጻቸው እንዳጋሩት ከሆነ በትግራይ ክልል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የህወሓት “ትላልቅ” ባለስልጣናትን ሳይቀር በመሪነትና በቀስቃሽነት ያካተተ እጅግ አሳፋሪ ፀረ-ህዝብ ዘመቻ ተጀምሯል፡፡

እንደ አቶ ነብዩ ገለፃ ይህ እጅግ አሳፋሪ ፀረ-ህዝብ ዘመቻ እስካሁን በመቐለ 70-እንደርታና በተንቤን የሚገኙ ክፍለ ከተሞች፣ ቀበሌዎችና መንደሮች የተጀመረ ሲሆን በዘመቻው ነባር ታጋዮችንና ካድሬዎችን በመሰብሰብ አላሰራ ያሉን የብልፅግና ደጋፊዎችና አባላት ናቸው ያሏቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በስብሰባ መሃል በማንበብና ቤተሰቦቻቸው አንድ በአንድ እየተጠሩ ተሰብሳቢው ፊት እንዲቆሙና ክፉኛ እንዲወቀሱ በማድረግ ሃላቀር የማሸማቀቅ ተግባር እየተፈፀመባቸው ይገኛል፡፡

በተለይ በመቐለ ክፍለ ከተማ ኲሓ በምትባለው አካባቢ አቶ ስዩም መስፍንና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር በአካል በመምጣትና ስብሰባዎችን በመምራት መንቀሳቀሻና መተንፈሻ ያሳጡን የብልፅግና ደጋፊዎችና አባላት ናቸው ያሏቸውን ሰዎች ዝርዝር እንዲነበብ ከተደረገ በኋላ እነዚህ ባንዳዎች ናቸው እንደሚባሉ አቶ ነብዩ ገልጸዋል፡፡

እነዚህና መሰሎቻቸው በጉያችን ውስጥ እያሉ የክልል ምርጫ ማካሄድ እጅግ አስቸጋሪ ነው፤ ስለሆነም ከአሁን ጀምራቹ አሸማቅቋቸው፣ በሏቸው፣ አሳዷቸው እንዲሁም ቃል-በቃል ግደሏቸው በማለት እጅግ አሳፋሪና ሃላቀር ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ሰንብተዋል እንዲህ አይነቱን ስብሰባ ያካሄዱት አቶ ስዩም መስፍንና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ስብሰባ በመሩባቸው መድረኮች ሳይቀር ጠንካራ ጥያቄዎችና ተቋዉሞዎች እየገጠማቸው መሆኑንም አቶ ነብዩ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በመቐለ ከተማ የብልፅግና ደጋፊዎችና አባላት ናቸው ተብለው እርምጃ እንዲወሰድባቸው በስብሰባ ውስጥ ከተፈረደባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ከአልጋ መውረድ የማይችሉና የቆረቡ የ80 ዓመት እናትና ከሞቱ አያሌ ወራት ያስቆጠሩ ገበሬ ስሞች መካተታቸው የተለየ አግራሞት ፈጥሯል፡፡

በዚህም በስብሰባ የተገኙት ለህዝብ የወገኑ ነባር ታጋዮችን ጨምሮ የአከባቢ ወጣቶችና ህዝቡ “የትግራይ ህዝብ ያካሄደው መራራ ትግልና ከባድ መስዋእት ለዚህ አሳፋሪ ሃላቀርነትና አምባገነንነት ነበር ወይ!” በማለት ተቋውሞአቸው እያሰሙ ይገኛሉ ስለሆነም ነገሮች በዴሞክራሲያዊና ህዝብና አገር ባስቀደመ ሃሳብና ተግባር እንዲታረሙ እንዲሁም የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉት ሲሉ አቶ ነብዩ እጅግ አሳፋሪ ዘመቻ በሚል ባሰፈሩት መልዕክታቸው አሳስበዋል፡፡