አባይ ሚዲያ ሃምሌ 08፤2012

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2012 ዓም ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ካፀደቃቸው አዋጆች መካከል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ማቋቋሚያ የሚያሻሽለው አዋጅ መሆኑ ታውቋል የፀደቀው አዋጅ በመግቢያ ምዕራፉ ማቋቋሚያ አዋጁን ለማሻሻል የተፈለገበትን ምክንያትም ሲያስቀምጥ‹‹የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተቋቋመበትን የሰብዓዊ መብቶችን ግንዛቤ የማስፋፋት፣ የማስጠበቅና የማስከበር ሥራ በተገቢው መንገድ እንዲያከናውን ማስቻልና የማስፈጸም አቅሙን ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤›› ይላል።

‹‹የኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ በኮሚሽነሮች ጉባዔ ውሳኔ መሠረት፣ በማናቸውም ሥፍራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ወይም እንደ ሁኔታው አቤቱታ መቀበያ ማዕከሎች ሊኖሩት ይችላል፤›› በሚል እንዲሻሻል ተደርጓል ከላይ የተገለጹት ማሻሻያ ድንጋጌዎች ፋይዳን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ፣  የሰብዓዊ መብት ጉዳይን የሚከታተሉ አመራሮች በቅርንጫፍ አካባቢ ክልሎች ፖለቲካ እንዳይሳቡ ለመከላከል፣ የልዩ ልዩ ሰብዓዊ መብት ዘርፎች ኮሚሽነር ሆነው እንዲመደቡና በዚህም ግንኙነታቸው ከሚከታተሉት ልዩ የሰብዓዊ መብት ጋር እንዲዛመድ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል።

ማሻሻያው ከአራት ያላነሱ የልዩ ልዩ ሰብዓዊ መብቶች ዘርፍ ጉዳዮችን የሚመሩ ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩ የሚደነግግ ሲሆን፣ የእነዚህን የዘርፍ ኮሚሽነሮች ሥልጣንና ተግባርንም በሚከተለው መሠረት ደንግጓል በዚህም መሠረት የዘርፍ ጉዳይ ኮሚሽነሮች በዋናው ኮሚሽነር አማካይነት የሚመደቡበትን የሥራ ዘርፍ በኃላፊነት ከመምራት በተጨማሪ፣ ከዋናው ኮሚሽነር ጋር በመመካከር የሥራ ዘርፉን ማደራጀት፣ ማስተዳደር፣ የሥራ ዘርፉን ሠራተኞች መከታተልና መምራት፣ የሚመሩትን ዘርፍ ወቅታዊና ዓመታዊ ክንዋኔ ሪፖርት ለዋና ኮሚሽነሩ ማቅረብና በዋና ኮሚሽነሩ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።

ሌላው አዲስ ድንጋጌ ሆኖ የቀረበው ደግሞ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውንም ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች ወይም በቁጥጥር ወይም በዕገታ ሥር የሚገኙ ሰዎች ያሉበትን ሥፍራ፣ እንዲሁም እንደ ትምህርት ቤትና መጠለያ ጣቢያዎችና ሌሎች ሥፍራዎች ያለ ቅድመ ማስታወቂያ መጎብኘት፤›› የሚል አዲስ ድንጋጌ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 13 ሆኖ ተደንግጓል።

ስለኮሚሽነሮች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች፣ እንዲሁም  በተጨማሪ የሙያ ሥራ መሳተፍ እንዲችሉ የሚቻልበትን ሁኔታ የሚፈቅድ ድንጋጌ በማሻሻያው እንዲካተት ተደርጓል በዚህም መሠረት የዋና ኮሚሽነሩ፣ የምክትል ዋና ኮሚሽነሩና የሌሎች ኮሚሽነሮች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች እንደ ቅደም ተከተላቸው በሚኒስትር፣ በምክትል ሚኒስትርና በዋና ዳይሬክተር ማዕረግ ላሉ የመንግሥት ተሿሚዎች የተፈቀዱ መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች እንዲያገኙ ተደንግጓል ተሿሚ ኮሚሽነሮች ልዩ አስተዋጽኦ ማድረግ በሚፈልጉበት የጥቅም ግጭት የማይፈጥር ሌላ የሥራ ወይም የሙያ መስክ ቢኖር፣ከኮሚሽነሮች ጉባዔ በሚቀርብ ሐሳብ መሠረት ከምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ጋር በመመካከር ሊፈቀድ እንደሚችልም በማሻሻያው ተደንግጓል።