አባይ ሚዲያ ሃምሌ 08፤2012

የፌደራል መንግስቱ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ጋር ግድያ ጋር በተያያዘ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ በተለይም በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ ሚዲያዎች፤ የጸጥታ ሃይሎች እና በርካታ ተጠርጣሪዎች ላይ የተወሰዱ አርምጃዎች ምናልባትም ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ወደ ሀገር መሪነት ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከፍተኛ የሚባል እስር ነው፡፡

መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ላሉ ቀውሶች ተጠያቂ መደረግ ያለበት ብልጽግና ፓርቲ ዘራፊ ቡድን ብሎ የጠራው ህወሃት መሆኑን እንደ አቋም በያዘበት የባለፈው የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ህወሃትና እንደ ፈለገ የሚጋልባቸው ሆድ አደር ቅጥረኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ሀገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደዋል ብሎ ነበር፡፡

በመሆኑም ህወሃትን በሚመለከት ብቻ በወሰዳቸው እርምጃዎች ግጭት እንዲባባስ መረጃ አሰራጭቷል ያለውን የክልሉን ቴሌቪዥን ከመዝጋት እስከ ሁለት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በቁጥጥር ስር እስከማዋል የደረሰ የእርምጃ ጅማሮ እየታየ ነው በአንጻሩ ህወሃት በተደጋጋሚ በሰጣቸው መግለጫዎች የፌደራል መንግስቱ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች የጠ/ሚ ዐቢይን የስልጣን ዘመን ከማሳጠርና ወደ ውድቀት ከመክተት ያለፈ ፋይዳ የለውም የሚል ዘለፋ አዘል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በዚህም የተዘጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱና የታሰሩ አመራሮቹ በአስቸኳይ ይፈቱ ብሏል ያም አለ ይህ ግን የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ሲታይ የጦርነት ቅስቀሳው በባሰ ሁኔታ መቀጠሉን የሚያሳዩ ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉ ነዋሪዎች ለአባይ ሚዲያ ተናግረዋል በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በቀበሌ አስተዳደር የሚገኙ አመራሮች ሳይቀሩ ህዝቡን በመሰብሰብ ለጦርነት ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትና እድሚያቸው ለጦርነት የደረሱ ወጣቶችን ለክልሉ መንግስት እንዲሰጥ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ የሚገልጹት ነዋሪዎች ወቅታዊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻው ወደምን ያመራ ይሆን የሚል ስጋት መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

በወልቃይት አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ለአባይ ሚዲያ እንደተናገሩት ከሆነ ከጦርነቱ ቅስቀሳ በአንጻሩ ህዝቡ የህወሃትን አስተዳደርን በቃህ ሊለው እንደሚገባና የጦርነት ቅስቀሳው እንደማይበጀው የሚገልጹ በራሪ ወረቀቶች እየተሰራጩ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል ይህ በእንዲህ እንዳለ የጦርነት ቅስቀሳው ላይ ተቃውሞ ያሰሙና ከእነሱ ግንኑኘት አላቸው የተባሉ ግለሰቦች በወልቃይት፤ በሽሬ፤ በተምቤንና በሌሎች የተለያዩ አካባቢዎች የጅምላ እስሮችና እንግልቶች እየተፈጸሙ ነው ያሉት የአይን እማኞች ከፍተኛ አፈናው መቀጠሉን ያብራራሉ፡፡

በህወሃትና በብልጽግና መካካል ያለው ተቃርኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ ዛሬ ላይ ቢደርስም ከድርድርና ከስምምነት ያለፈ ለሚመስለው የሰፋ ቁርሾ ምን መፍትሄ ይመጣል የሚለውና መንግስት በህወሃት ላይ በሚወስዳቸው እርምጃዎችም ይሁኑ ህወሃት ህዝቡን በሚቀሰቀስበት አግባብ ንጹሃን ላይ ምንም ጉዳት መድረስ የለበትም የሚለው መነጋገሪያና መወያያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡